የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተቋሙ ዓላማ ፈጻሚ የቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል
April 12, 2023
ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን ዓላማዎች ከመፈጸም አኳያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር፤ የጤና ላብራቶሪዎች አቅም ግንባታ እና የማጣቀሻ ምርመራዎች፤ የህብረተሰብ ጤናና ሥርዓተ-ምግብ ችግሮች፣ ፕሮግራሞችና ስትራቴጂዎች ምርምር፤ እንዲሁም የጤናና ጤና ነክ መረጃዎች ቅመራና ትንተና ስራዎችን አስመልክቶ ከተቋሙ ዓላማ ፈጻሚ የቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ውይይቱ የተመራው በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራር ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ውስጣዊ አሰራር፣ ቴክኖሎጂና ዲጂታይዜሽን አጠቃቀም፣ አንኳር ጉዳዮች/ፍላግሺፕ ኢንሼቲቭስ፣ ከአጋር ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት፣ ቅንጅታዊ አሰራርና መናበብን በተመለከተ ምክክር ተደርጓል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ምክትል ዋ/ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያዬቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሁሉም የስብሰባው ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነቶች በአዲስ መንፈስና ተነሳሽነት በመወጣት የኢንስቲትዩቱን “የአፍሪካ የህብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል መሆን” ራዕይ ለማሳካት እንደሚተጉ በመግለፅ የጋራ መግባባት ተደርሶ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡