የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በፆታዊ ጥቃት፣ የህፃናት መብትና ደህንነት እንዲሁም የእብድ ዉሻ በሽታ (Rabies) ዙሪያ ከአዲስ ከተማ ክ/ከተማ እና ከጉለሌ ክ/ከተማ ለተወጣጡ ባለሞያዎች በኢንስቲትዩቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል
በቦታው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት (ሴ/ህ/ወ/ጉ) ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ማርታ አበራ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና ምላሽ የመስጠት፣ የተለያዩ
የምርምር ስራዎችንና የሪፈራል ላብራቶሪ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ጠቁመው ከክፍለ ከተሞች ጋራም ብዙ ስራዎች በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የህጻናትን መብትና ደህንነት መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት እንደሆነ ገልጸዉ ህጻናት ልጆች መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ፣ ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ እና የነገ
ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንዲሆኑ ሁላችንም በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በከተማችን በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን አስቀድመን መከላከልና ጥቃት ተከስቶም ሲገኝ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ፣ ህክምና እንዲሁም የስነልቦና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው በተጨማሪም የህግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙና አጥፊወችም አስተማሪና ተገቢዉን ቅጣት እንዲያገኙ መደረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ በመሆኑ በጋራ መስራት አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies) በተመለከተ ማህበረሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚስፈልግም አክለዋል፡፡
በመድረኩም የፆታዊ ጥቃት እና የህፃናት መብትና ደህንነት ዙሪያ ከሴቶች የህግ ባለሙያ ማህበር ወ/ሪት ሰላማዊት ደሳለኝ እንዲሁም የኢንስቲትዩቱ ባለሙያ አቶ አበበ ጌታቸው በእብድ ዉሻ በሽታ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል።