የኢትዮጵያ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ፕሮግራም ዓለም አቀፍ እውቅናን አገኘ
የጤና ሚኒስቲር ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከተለያዩ የአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የመካከለኛ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጣኞች ምርቃት እና በዓለም አቀፍ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም ህብረት (TEPHINET) የተገኘውን አገር አቀፍ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ እውቅናን በተመለከተ ከፍተኛ አስትዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት የምስጋና ፕሮግራም በዛሬው እለት አካሄደ::
ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ የስልጠና ፕሮግራም በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከላት ውስጥ ያለውን የባለሙያ ክፍተት በመሙላቱ በኩል እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ደረጄ በሕብረተሰብ ጤና ልዩ ልዩ ስራዎች ውስጥ የተለያዩ የጤና ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት በመለየትና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ብሎም የቅኝት ስራዎችን በመስራት እንዲሁም መረጃን መሰረት ያደረጉ የጤና ችግሮችን በመለየትና ፈጣንና ቀልጣፋ ሪፖርት በማድረጉ በኩል የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ምሩቃን ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
ሚንስትር ዴኤታው አያይዘው የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ፕሮግራም ውጤታማ ከሆነባቸው ተግባራት መካከል አንዱ አለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ ሲሆን ይህም ውጤት የተሳካ ይሆን ዘንድ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከላት በአጠቃላይ ሕብረተሰቡ እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ እና አጋር አካላት ትብብር መሆንን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው አገር አቀፉ የፊልድ ኢፕዲሞሎጂ ፕሮግራም ውጤታማ ይሆን ዘንድ አስተዋጽኦ ያደረጉትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል፡፡ ዶ/ር መሳይ በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎችን በማብቃቱና በማፍራቱ በኩል ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ይህም አለማቀፍን የጤና ሽፋን በማሳካቱ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ እንዳደረገ አውስተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የፊልድ ኢፕዲሞሎጂ እና የላቦራቶሪ ስልጠና ፕሮግራሞች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመከላከሉ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ከመግለጻቸውም በላይ ስልጠናው የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በማቃኘት፣ በመለየት፣እና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በኩል እያተከናወኑ ያሉትን ልዩ ልዩ ስራዎች አቅም እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ዘገየ ኃይለማሪያም አገር አቀፍ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና አስተባባሪ የስልጠናውን አጠቃላይ ፕሮግራም በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን አቶ ተስፋዬ ድጋፌ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና እውቅና ፕሮግራም አስተባባሪ በበኩላቸው ደግሞ የእውቅናው ፕሮግራም ዓላማና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ጠቀሜታ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ከሁሉም ክልል ተመርጠው ለዘጠኝ ወራት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠናን ውስደው ያጠናቀቁ 19 ባለሙያዎች ስልጠናውን ለማጠናቀቃቸው ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ የመመረቂያ ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና በአገር አቀፍ ደረጃ አለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ ከመሆኑም በላይ የፕሮግራሙ ቴክኒካል ዳይሬክተር በመሆንም እያገለገለ ይገኛል፡፡
በእውቅናው ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የምርምር ተቋማት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ አጋር ድርጅቶች እና አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት የእውቅና ስርተፍኬት የተሰጣቸው ሲሆን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አገር አቀፉ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ እና የላቦራቶሪ ስልጠና ፕሮግራም ውጤታማ እና የተሳካ ይሆን ዘንድ ዘወትር እያደረገ ላለው የቴክኒካል ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር በኩል እውቅና ተሰጥቶታል፡፡