የኢንሰቲትዩቱ የሰራተኞች ካፌና ሬስቶራንት ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የሶስት ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ አከናወነ፡፡
![የኢንሰቲትዩቱ የሰራተኞች ካፌና ሬስቶራንት ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የሶስት ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ አከናወነ፡፡](https://ephi.gov.et/wp-content/uploads/2021/03/hudase-gebta.jpg)
ዶ/ር ኤባ አባተ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የቦንድ ግዢው በተከናወነበት ስነ ስርዓት ላይ እንዳስታወቁት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እና ስራ ላይ መዋል እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ ለጤናው ዘርፍ የሚሰጠው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ እንደሆነ መረጃዎችን በማጣቀስ አብራርተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ በግድቡ ጠቀሜታ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፎችን አጥንቶ ማቅረቡን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ከህብረተሰባችን ውስጥ 55% በላይ የሚሆነው ህዝብ የኤሌክትሪክ ሀይል የማይጠቀም በመሆኑ በቤት ውስጥ በሚከሰት የአየር ብክለት የተነሳ ለሳንባ ምች፣ ለሳንባ ካንሰር፣ ለልዩ ልዩ ከመተንፈሻ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች፣ ለልብ ህመምና ለሌሎችም በርካታ ህመሞች ተጋላጭ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 ብቻ ከላይ በተጠቀሱት በሽታዎች በአንድ ዓመት ብቻ 67000 ዜጎቻችን ለሞት የተዳረጉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ባፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቻችን በቤት ውስጥ በሚከሰተው የአየር ብክለት ጠንቅ የተነሳ በልዩ ልዩ በሽታዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሃይሉ አብርሃም በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የኮሮና ቫይረስን የተመለከቱ በርካታ የመከላከል ስራዎቸንም እያከናወነ ጎን ለጎን የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያግዝ የቦንድ ግዢ በማከናወኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህም ሰራተኛው ያለውን ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡