የኢንስቲትዩቱ ሴቶች ፎረም ለአባላቱ ስልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ከሴቶች ፎረም ጋር በጋራ በመሆን ለ20 የፎረሙ አባላት፣ለ30 አጋር ወንዶች፣ በአጠቃላይ ለ50 ሰዎች የሴቶችን የአመራርነት ክህሎት ስለ ማሳደግ፣ ስለ ሁለንተናዊ የልጆች አስተዳደግ እንዲሁም ኮቪድ በሴቶች ላይ እያደረሰ ስላለው ተፅዕኖ በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ከሰኔ 11- 12/ 2013 ዓ/ም የቆየ ስልጠና በአዳማ ከተማ አካሄደ።
በስልጠናው መጀመሪያም በሞት የተለዩትን የቀድሞ የኢንስቲትዩቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለነበሩት ወ/ሮ ኑሪያ ዩሱፍ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
በስልጠናው የተገኙት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት የሴቶች እና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር ወ/ሮ የሮም ሞረዳ እንደገለፁት ሰልጣኞቹ ከዚህ ስልጠና በኋላ ስለ ልጆች አስተዳደግ፣ ልጆችን በአእምሮ ማጎልበት አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር በቂ ግንዛቤ፣ እንዲሁም በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ስራቸውን በሃላፊነት፣በታማኝነት እና በቅንነት በብቃት ማሸነፍ እንዲችሉና የራስ መተማመናቸው እንዲጨምር የሚያስችል ስልጠና መሆኑን ጠቁመው ከኮቪድ ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር እንዲሁም በሴቶች ላይ እያሳደረ ያለው ተፅእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንንም በመቀነስ እራሳቸውን ብሎም ቤተሰባቸውን በተገቢው መልኩ መንከባከብ እንደሚገባ ግንዛቤ የሚወስዱበት ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል።