የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬትና የጨቅላ ህጻናት ኤች አይ ቪ ምርመራ ትግበራ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጀመረ፡፡
የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬት እና የጨቅላ ህጻናት ኤች አይ ቪ ምርመራ ትግበራ ላይ ያተኮረ አመታዊ የስራ አፈጻጸም አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ ተጀመረ፡፡
አቶ ፍቃዱ ያደታ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የፕሮግራም ዘርፍ ጽ/ቤት ኃላፊና አማካሪ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኤች አይ ቪ/ ኤድስ በሀገራችን መከሰቱ ከታወቀበት ጀምሮ ስርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አውስተው ባለፉት አመታት በተደረጉት ጥረቶች በኤች አይ ቪ አዲስ የመያዝ ምጣኔ እኤአ በ2010 ከነበረው 46 በመቶ በኤድስ ምክንያትየሚከሰት የሞት መጠን ደግሞ በ52 በመቶ የቀነሰ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ አብራርተው የቫይራል ሎድ ምርመራ አገልግሎት ሽፋንንም ለመጨመርና የአገልግሎቱን ጥራት ለማሻሻል ልዩ ልዩ ስራዎችን እየተከናወኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደ ሀገር የተቀበለችውን የአለም አቀፍ የ2030 ኤች አይ ቪ ግብ እንዲሁም የ3ቱን 95ን ግብ ለማሳካት ትብብርን፤ ቅንጅትን እንዲሁም አጋርነትን ባጠናከረ መልኩ በጋራ መስራት ወሳኝ በመሆኑ ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የዕለቱ የክብር እንግዳ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለሶስት ቀናት የሚቆየው ይህ አውደ ጥናት ባለፈው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሎድ መጠን ልኬት እና የጨቅላ ህጻናት ኤች አይ ቪ ምርመራ አገልግሎትን በተመለከተ በተመዘገቡ መልካም ውጤቶች እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ምክክር በማድረግ የወደፊት አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አውደ ጥናቱ የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬት እና የኤች አይ ቪ ምርመራ አገልግሎትን የማጠናከር ስራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን ከፍ ማድረግ የሚቻልበትን ስልትና ዘዴዎች እንዲሁም የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትብብር በተዘጋጀው በዚህ አውደ ጥናት ላይ ልዩ ልዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተካፋይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡