የእብድ ውሻ በሽታን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ
የኢንስቲትዩቱ የፓራሳይቶሎጂ፣የባክትሮሎጂ እና የእንሰሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት የእብድ ውሻ በሽታን አስመልክቶ የካቲት 2/2012ዓ.ም የጤና ሚኒስቴር ድኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የፓርላማ አባላት በተገኙበት በእንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ፡፡
የመድረኩ ዋና አላማ በእብድ ውሻ በሽታ ዙሪያ እተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎችን ማሳየት እንዲሁም ክትባትን እና ተየያዥነት ያላቸውን የግብዓት አቅርቦት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ያሉ ክፍተቶች ምን እንደሆኑ በመግለጽ በቀጣይ በሃገር አቀፍ ደረጃ የውሻ በሽታን ለማጥፋት የተዘጋጀውን እቅድ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመድረኩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት የእብድ ውሻ በሽታ የበርካታ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈ፣ እንሰሳት ለሰው ልጆች በርካታ ጥቅሞችን የሚሰጡ ቢሆኑም 60 በመቶ ሚሆኑት ሰውን የሚጎዱ በሽታዎች የሚተላለፉት ከእንሰሳት መሆናቸውን ከነዚህም ውስጥ አንዱ የእብድ ውሻ በሽታ መሆኑንና ከ70 እስከ 80 ፐርሰንት ውሾችን በመከተብ በሽታውን ማጥፋት እንደሚቻል ጥናቶች እንደሚያሳዩ ከመግለጻቸውም በላይ በ2020 በሽታውን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የተያዘውን እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ደረጃ ሁሉም በቅንጅት በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ በጤና ሚኒስቴር ስም ለባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ኤባ አባተ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ የተሰጡትን ሃላፊነትና ተግባራት ከማቅረባቸውም በላይ በቅርቡ በአለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ የወፍ ጉንፋን፣የኢቦላ እና ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ከእንሰሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውንና እነዚህ በሽታዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የሚፈጥሩ መሆናቸውን ነገር ግን በተናጠል መከላከል የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብርና አገልግሎት የሚጠይቁ እና ኢንስቲትዩቱ ከእንሰሳት ወደ ሰው ሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከባለደርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ስለ እብድ ውሻ በሽታ በሰው ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት አስመልክቶ ድራማዊ ትዕይንት፣የተለያዩ የጥናት ውጤቶችና አሁን በሃገር ደረጃ በሽታው እያደረሰ ያለውን ጉዳት በቀጣይ ስለሚሰሩ ተግባራት በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው በሽታውን ለማጥፋት ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነትና ተግባራት ሊወጣ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የህዝብ ምክር ቤት ተወካይ አባላት፣የመንግስት ተቋማት ሃላፊዎች፣የክልል መንግስታት መስሪያ ቤት ተወካዮች፣የልማት አጋር ድርጅቶችና ተጋባዥ እንግዶች በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡