የእናቶችና ህጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎችን አስመልክቶ የናሙና ምዝገባ ሥርዓት የማስጀመሪያ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር የእናቶችና ህጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎች እንዲሁም አጠቃላይ የበሽታ ሰርጭት የመለየት እና ያሉትን የክትትል ስርዓቶች ለማጠናከር የናሙና ምዝገባ ስርዓትን (Sample Registration System/SRS/) ለመዘርጋት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን የማስጀመሪያ የዉይይት መድረክም ሰኔ 24/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት በኢትዮጵያ የወሊድ ሁኔታ የእናቶችና ህጻናት ሞት እና የሞት መንስኤዎችን ለመለየት የናሙና ምዝገባ ስርዓትን መዘርጋት ዘላቂ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና ውሳኔ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን አመላክተው፤ እየተካሄደ የሚገኘው የናሙና ምዝገባ ሥርዓት የማስጀመሪያ ፕሮግራም እና የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ በቀጣይ በቅንጅት መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በመተንተን፣ መረጃዎችን ተደራሽ በማደረግ እና በማጋራት፣ የተሻሉ የጤና ግንባታ ስራዎች የሚመዘገቡበት በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በቅንጅት መስራታቸው እጅግ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራ ትንተና ማዕከል ያከናወናቸው ተግባራትን አስመልክቶ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶች በመድረኩ ቀርበዉ ዉይይት የተደረገባቸዉ ከመሆኑም በተጨማሪ የናሙና ምዝገባ ስርዓት (SRS) በመዘርጋት የመረጃ ክፍተቶች እንዳይኖሩ በማድረግ በሀገሪቷ ያለውን የጤና ልማት እና ኢንቨስትመንት እቅድ ለማሳካት እንዲሁም በማስረጃ የተደገፈ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚረዳ ፕሮግራም መሆኑን በመድረኩ የቀረበ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ የአፍሪካ ሲዲሲ፣ ጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሌሎች አጋር ድርጅቶች በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል።