የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝትና ምላሽ ስርዓትን ማጠናከር መከላከል በምንችልባቸው ምክንያቶች የሚከሰቱ ሞቶችን ለመቀነስ ያስችላል
የእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ ስርዓትን በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ ከክልል ጤና ቢሮና ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአጋር ድርጅት ኃላፊዎች እና ተወካዮች ጋር ውይይትና ምክክር ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክትር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ እደተናገሩት መከላከል በምንችልባቸው ምክንያት የሚከሰቱ የእናቶች እና የጨቅላ ህጻናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ (MPDSR) ዙሪያ ያሉትን አፈጻጸሞች እና ክፍተቶች በማየት በቀጣይ የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ለተግባራዊነታቸው እንድንረባረብ ታስቦ የተዘጋጀ የማነቃቂያ መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ህመምና ሞት ለመቀነስ በጥናት የተደገፉ አሰራሮችን እየተገበረች እንደምትገኝና የእናቶች ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት አንደኛው እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር መሳይ ይህም የሞት መረጃዎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ሌሎች እናቶች በተመሳሳይ ምክንያት እንዳይሞቱ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሰራር በመሆኑ እጅግ ውጤታማ አሰራር ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተቀናጁ ስራዎች በወሊድ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞትን ምጣኔን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ቢቻልም አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እናቶች መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች ይሞታሉና የሞት ሪፖርቶችን በፍጥነት በማሳወቅና ምላሽ በመስጠት በተመሳሳይ መንስኤዎች ምክንያት የሚከሰቱ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ በቅንጅት መስራት ይገባናል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ናቸው፡፡
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው የእናቶችንና ህፃናትን ጤንነትን መጠበቅና ሞታቸውን መቀነስ የሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መገለጫ የሚያመለክት በመሆኑ የጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየሰራ እንደሆነና ለያዝናቸው እናቶችና ህጻናት ጤና ግቦች መሳካት ሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝትና ምላሽ ስርዓት አገራዊ ሁኔታ እና እየተሰሩ ያሉ የምላሽ ስራዎች ለውይይት ቀርቦ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ የክልል ጤና ቢሮና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአጋር ድርጅት ኃላፊዎች እና ተወካዮች የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝትና ምላሽ ስርዓት በሚጠናከርበት ዙርያ ሀሳብና አስተያየቶችን በማንሳት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡