የእናቶች አዲስ የተወለዱ ህፃናትን ጤና ለማሻሻል የተዋቀረ የህክምና አግልግሎት ጥራት ትስስር ዙሪያ ምክክር መድረክ ተካሄደ።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤና እና ስነ ተዋልዶ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የጤና አገልግሎት ጥራት ትስስር (Quality Of care Network(QCN) ) ላይ ሲያካሂድ የነበረው ጥናት የመጀመሪያ ዙር በመጠናቀቁ ጥናቱ ያለበትን ሂደት ለማሳወቅ በአዲስ አበባ ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የአውደ ጥናት መድረክ ተካሂዷል።
ፕሮግራሙንም በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት ጥራት ዳሬክቶሬት ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ደሳለኝ በቀለ በመግቢያ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም በጥናቱ የተሳተፉ አካላት ላገኙት ግኝት ልባዊ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
የጥናቱ ዋና አላማ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የህክምና አገልግሎት ጥራት ትስስር የአሰራር ሂደት ማየት እና የትስስሩን የጋራ አጀንዳን መፍጠር ፣ የአስተዳደሩን ባለቤትነት ማሳካትና አካባቢያዊ እሴት ያላቸው መፍትሄዎችን በሃገሪቱ በጤና ተቋማት ያሉ እናቶች እና አዲስ የተወለዱ ህፃናት ሞትና ሞተው የሚወለዱ ህፃናትን ቁጥር በ 5ዓመታት ውስጥ በ50 % ለመቀነስ የታሰበውን ግብ ለማሳካት ከማበርከት አንጻር የትኞቹ ሁኔታዎች (የታቀዱና ያልታቀዱ) እንደጠቀሙ ወይም እንቅፋት እንደሆኑ ማሳየት መሆኑን ከመድረኩ ተገልጿል ።
በስርዓተ ጤና እና ስነተዋልዶ ጤና ምርምር ዳሮክቶሬት ተመራማሪ አቶ ገረመው ጎንፋ በተደረገው ጥናት ዙሪያ የተገኘውን ግኝት ሰፋ ባለ መልኩ አቅርበዋል፤ በቀረበው የሂደቱ ሪፖርት ዙሪያ የተገኙ አካላት ሀሳብ አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን ለተነሱ ሀሳቦችም የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ በመስጠት መድረኩን እጠናቀዋል።