የክልል የላብራቶሪ ግንባታ ስራዎችን በተመለከተ የስራ ጉብኝት ተካሄደ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በመገንባት ላይ የሚገኙ የሪጅናል ላብራቶሪዎች አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡
የሀገር አቀፉ ህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ፎረም ተሳታፊዎች በዛሬው ዕለት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፡ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት እና በዓለም ባንክ በጋራ እየተገነቡ የሚገኙትን ዘመናዊ የሪጅናል ላብራቶሪ ግንባታ ስራዎች ሂደትን በተመለከተ በከፋ ዞን የገብረጻዲቅ ሸዋ አጠቃላይ ሆስፒታል እና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል በመገኘት በጎበኙበት ወቅት እንደተገለጸው የሁለቱ ሆስፒታሎች የሪጅናል ላብራቶሪዎች ግንባታ ስራ በሚጠናቀቁበት ወቅት ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ ይላኩ የነበሩ ናሙና ምርመራዎች በነዚህ ላብራቶሪዎች ስለሚሰሩ ለህሙማን የሚሰጠውን ግልጋሎት ይበልጥ እንደሚያቀላጥፈው ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ፍቅረማርያም ጳውሎስ የገብረጻዲቅ ሸዋ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ እና ዶ/ር እርቅይሁን ጳውሎስ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሪጅናል የላብራቶሪ ግንባታ ስራዎች መጠናቀቅ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎችም እፎይታ መሆኑን አስረድተው የላራቶሪዎቹ ግንባታ መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በአስፈላጊው ግብአቶች መሟላታቸው ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን ግልጋሎት ከፍ እንደሚያደርገውና የታካሚውንም እንግልት እንደሚቀንስለት ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ከሁለቱ ሆስፒታሎች ጉብኝት በኃላ የላብራቶሪዎቹን ግንባታ ስራዎች የኢንስትቲዩቱ ማኔጅመንት በቅርበት በመከታተል ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ም/ዋና ዳይሬክተር እና የማናጅሜንት አባላት የተገኙ ሲሆን ከጉብኝቱ በኃላ በተደረገው ውይይት ያጋጠሙ ችግሮች እና ተግዳሮቶች ላይ እንዲሁም ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሰፋ ያለ ውይይቶች ተደርገው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡