የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች አፈጻጸም እያደገ መጥቷል

የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች አፈጻጸም እያደገ መምጣቱ ተነገረ::
የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች በ2018 ዓ.ም የጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ፣ የበሽታ ቅኝት፣ የላቦራቶሪ ምርመራና የምርምር አቅማቸውን በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ገለጹ። ይህን ያስታወቁት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸማቸውን ሲያቀርቡ ነው።

የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ፣ ኢንስቲትዩቱ በ2018 ዓ.ም ካቀዳቸው ሥራዎች ከ95 በመቶ በላይ ማሳካቱን ገልጸዋል። ክልሉ በተለይም በዲጂታል የታገዙ የላቦራቶሪና የጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ የአንድ ጤን አገልግሎት እና መሰል የሕብረተሰብ ጤና አቅሞችን ከማሳደግ ባለፈ የምርምር ሥራዎችን ማጠናከሩን ጠቁመዋል።
የሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ፣ ማርበርግን ጨምሮ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመመከትና ለመቆጣጠር የተቀናጀ የምላሽ ሥርዓት መጠናከሩን ገልጸዋል። በበሽታ ክትትልና ምርመራ፣ በግንኙነት ክትትል፣ በማኅበረሰብ ተሳትፎና በአደጋ ምላሽ አቅም ላይ የተገኙ ውጤቶች ለቀጣይ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት ጠንካራ መሠረት መሆናቸውን አስረድተው፣ ኢንስቲትዩቱ በ2018 ዓ.ም ካቀዳቸው ሥራዎች 95 በመቶ በላይ ያህሉን ማሳካቱንም ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት በተለይም በቅርቡ የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ ለመቆጣጠር ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በክልሉ ተደጋጋሚ የጤና አደጋዎች መከሰታቸው የምላሽ አቅምን የበለጠ ማጠናከር እንዳስፈለገ ጠቁመው፣ ጠንካራ አመራርና ትብብር ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን አስረድተው በ2018 ዓ.ም 87% በላይ አፈፃፀም እንዳመጡ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀመዶ አህመድ በበብኩላቸው፣ ክልሉ በሞቃታማና በረሃማ አካባቢ እንዲሁም ከሁለት አገራት ጋር በሚዋሰን ድንበር ላይ በመገኘቱ ሊከሰቱ ለሚችሉ የጤና አደጋዎች ዝግጁነቱን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል። በቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ በሕብረተሰብ ጤና ቅኝት፣ በላቦራቶሪ ምርመራና በአደጋ ምላሽ አቅም ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዴንጉ ፌቨርና ኮሌራ ወረርሽኞች ላይ የተቀናጀ ምላሽ በመስጠት የወረርሽኝ ሞትን ወደ ዜሮ ማድረስ መቻሉን እና በአጠቃላይ በበጀት አመቱ ከ84.2% በላይ የስራ አፈፃፀም እንዳለው አስታውቀዋል።
የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶቹ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል አመራሮችና ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት በበሽታ ቅኝትና ምላሽ፣ በላቦራቶሪ፣ በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽንና በጤና አደጋ ዝግጁነት የተገኙ ውጤቶችን ለማጠናከር በቀጣይም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።