ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽን ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመች

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የጤና አደጋዎችን በጋራ ለመከላከል፣ በፍጥነት ለመለየትና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የትብብር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመች ሲሆን፤ ስምምነቱ “Strengthening Cross-Border All-Hazards Preparedness and Response in Africa: From Fragmented Action to Collaborative Resilience” በሚል የተዘጋጀ ሲሆን፣ የአፍሪካ አገራት ድንበር ተሻጋሪ የጤና ስጋቶችን በተናጠል ከመመለስ ወደ የተቀናጀ፣ የጋራ ዝግጁነትና ምላሽ ሥርዓት እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ነው።

የመግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ኮሚቴ 76ኛ ጉባዔ ላይ ጎን ለጎን በተካሄደ መድረክ ሲሆን፣ የተለያዩ አገራት የጤናው ዘርፍ አመራሮች በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (IGAD) ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ስምምነቱ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን ከጤና አደጋዎች ለመጠበቅና የክልሉን የጤና ደህንነት ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ኤምፖክስ፣ ኢቦላና ሌሎች መሰል የጤና አደጋዎች ድንበር ስለማይገድባቸው፣ የዝግጁነትና ምላሽ ሥራዎችም ከአገር አቀፍ ወሰን ባለፈ በጋራ መከናወን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ በኩል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን፣ የጤና አደጋዎች በድንበር ስለማይገደቡ የአገራትን የበሽታ ክትትል፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የጋራ ዝግጁነትና የምላሽ ቅንጅት ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል። በተለይም በድንበር አካባቢ የሚከሰቱ የጤና አደጋዎችን በፍጥነት መለየት፣ መረጃን በወቅቱ መለዋወጥና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተፈረመው ስምምነት የጋራ የጤና አደጋ ዝግጁነትን፣ የበሽታ ክትትልን፣ የመረጃ ልውውጥን፣ የምላሽ ቅንጅትንና የአገራትን ተቋማዊ አቅም ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደርጋል ያሉት ዶ/ር መሳይ፣ ይህም የጤና አደጋዎች በአንድ አገር ድንበር ተወስነው እንዳይቀሩ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልና ለመመለስ የሚያስችል የጋራ አቅም ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጤና ደህንነትን ለማጠናከር፣ ድንበር ተሻጋሪ የጤና አደጋዎችን በጋራ ለመቆጣጠርና የአፍሪካን የጤና ሥርዓት የበለጠ ተቋቋሚ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።