የክሪፕቶኮካል አንቲጅን (Cryptococcal Antigen/CrAg የላቦራቶሪ ምርመራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የክሪፕቶኮካል አንቲጅን (CryptococcalAntigen CrAg) የላቦራቶሪ ምርመራ ማስጀመሪያ ሥልጠና እና የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ታህሳስ 19 እና 20/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡
ይህ አገልግሎት በዋናነት ከኤች. አይ .ቪ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በኤች. አይ. .ቪ ቫይረስ ምክንያት ለሚከሰቱ ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመመርመር የሚያገለግል ሲሆን፤ በተለይ በክሪፕቶኮካል ሜኒንጃይቲስ (Cryptococcal meningitis) በተባለ ፈንገስ ምክንያት የሚመጣ እና በተለምዶ የማጅራት ገትር ተብሎ በሚጠራ በሽታ ምክንያት የሚከሰት ሞት እና ህመምን ለመቀነስ የዚህ ምርመራ መጀመር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት ሪፖርት ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በcryptococcal meningitis በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁ ሲሆን፣ በተለይ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ባለማገኘት ምክንያት ከሚከሰቱ ሞት ውስጥ ከ15% በላይ ለሞት መንስኤ እንደሆነ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በዚህ የላቦራቶሪ ምርመራ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የክልል ኢንስቲትዩት/የላቦራቶሪ ኃላፊዎች፤ የክልል ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ. ፕሮግራም ኃላፊዎች/ተወካዮች እና የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ይህንን አገልግሎት ለማስጀመር አስፈላጊውን የላቦራቶሪ ግብዓት በማሟላት ሂደት ውስጥ ትልቁን ሚና ለተጫወቱ ሲዲሲ ኢትዮጵያ፣ አይካፕ ኢትዮጵያ እና ሌሎችንም ባለድረሻ አካላት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልል ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ እና የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ አበበ በመክፈቻ ንግግራቸው አመስግነዋል፡፡
የምርመራ አገልግሎቱም ከዛሬ ጀምሮ በተመረጡ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች የሚጀመር ሲሆን፣ በቀጣይ በሁሉም ጤና ተቋማትን ለማስጀመር እየተሰራ ይገኛል፡፡