የክትባት ፕሮግራምና በክትባት የምንከላከላቸዉ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ የዘጠኝ ወር አፈፃፀም የጋራ የግምገማ መድረክ ተጠናቀቀ

በግምገማ መድረኩ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ የግምገማ መድረኩን ላዘጋጁት ምስጋናቸዉን በማቅረብ ንግግራቸዉን የጀመሩ ሲሆን በክትባት ዙሪያ ሰፊ ስራ መሰራቱን አስታዉሰዉ ክትባቱ ዉጤታማ መሆኑ የሚታወቀዉ ወረርሽኞች ማስቀረት ሲቻል መሆኑን አክለዉ ገልፀዋል፡፡መደበኛ ክትባት አገልግሎት እየተጠናከረ ያለ ቢሆንም በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ወረርሽኝ ተከስቷል ይህ የሆነበት በርካታ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ክፍተቱ ምን ላይ እንደሆነ ለይቶ የበለጠ ለመስራት እና ማህበረሰቡን ከወረርሽኝ ለመታደግ አብሮ በጋራ መገምገምና መነጋገር ያስፈልጋል የዚህ የግምገማ መድረክ ዋና አላማ ያለፈዉን ዘጠኝ ወር አፈፃፀም ምን እንደሚመስል እና ከፊታችን ባለዉ በጀት አመት እንዴት አቅደን ብንሰራ የማህብረሰባችንን ችግር ለመከላከል የምንችለዉ የሚለዉን በጋራ ለማየትና ለመወያየት ነዉ፡፡ይህ አይነቱ የጋራ ግምገማ በክልሎች ተጠናክሮ በመቀጠል እስከ ወረዳ ድረስ በመዉረድ የክትባት ፕሮግራምን አጠናክረን በጋራ በመስራት ዉጤታማ መሆን ይቻላል ስለሆነም ሁላችንም ለዚህ ስራ መዘጋጀት ይገባል እንደ አመራርም በየደረጃዉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸዉን ገልፀዉ ለተሳታፊዎች ምስጋና በማቅረብ መልካም የዉይይት የግምገማ ጊዜ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም ሃላፊ አቶ መልካሙ አያሌዉ እንደተናገሩት በዚህ መድረክ የተሰባሰብነዉ ሁላችንም በክትባት ፕሮግራም፣ በቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ፣ የክትባት ሴፍቲ፣የክትባት አቅርቦት(ሰንሰለት) ሁኔታዎችን በተመለከተ ተመሳሳይ ስራ አንድ አላማ ለማሳካት ቢሆንምግን ባለን አወቃቀር መሰረት በተለያዩ ክፍሎች ቦታዎች በየግል ስንሰራ ቆይተናል ስራችንን በተለያየ መገናኛ መንገድ መረጃዎችን እንለዋወጣን ዛሬ በተለየ ሁኔታ በዚህ ስፍራ የተገናኘነዉ ለበርካታ አመታት ስንሰራዉ የቆየነዉን የክትባት ሁኔታ ከየት ወዴት እየሄደ ነዉ ያለዉ፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ ምን ይመስላል፣ የዘጠኝ ወር አፈፃፀማችንስ እንዴት ነዉ፣አንዱ የስራ ክፍል ለሌላዉስ ምን እያበረከተ ነዉ፣ በቀጣይ እንዴት መስራት አለብን የሚለዉን በጥልቀት ተወያይተን ለምናገለግለዉ ማህበረሰብ ትርጉም ያለዉን ስራ እንዴት እንሰራለን የሚለዉን የምናይበት መድረክ ነዉ፡፡
በግምገማ መድረኩም ላይ የክልሎች/የከተማ አስተዳደሮች የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ቀርቦ ከተሳታፊዎች በተነሱ ሀሳቦችና አስተያየቶች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።