የኮሌራ ክትባት ዘመቻ በአማራ ክልል በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ ነው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በትላንትናው ዕለት ማለትም መጋቢት 21/2014 በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ከተማ ያስጀመረው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በተሳካ መልኩ እየተካሄደ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ክትባቱም እስከ መጋቢት 25/2014 የሚቀጥል ሲሆን ቤት ለቤት እና በተፈናቃዮች መጠለያ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ክትባቱ በዋነኛነት በቦታው የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
በክትባቱ ዘመቻ የማስጀመሪያ ንግግራቸው የአማራ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንደተናገሩት በክልሉ 135000 ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 5000 የሚሆኑት በስደተኛ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በላይ ደግሞ ያሉት በሕብረተሰቡ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ናቸው፡፡ እንደ አቶ በላይ ገለጻ ቀደም ብሎ ክትባት ለሚሰጡት ባለሙያዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን የክትባቱ ሂደትም በተሳካ መልኩ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
አቶ ችሎት ተቀባ የደባርቅ ከተማ ምክትል ከንቲባ በበኩላቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ በተለይ በተፈናቃዮች መጠለያ ሊፈጠር የሚችለውን ወረርሽኝ ግምት ውስጥ በማስገባት የበሽታውን ክትባት በደባርቅ ማስጀመር በመቻሉ ለዚህም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን በክልሉ ሕብረተሰብ ስም ማመስገን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ የክትባት ዘመቻውን ሲያስጀምሩ እንዳሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዓላማ በሽታ ከመፈጠሩ በፊት ቀድሞ መከላከል እና ቅድሚያ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን አከባቢዎች በመለየት የሚያስፈልገውን የቀድሞ መከላከል ስራ ማካሄድ እንደመሆኑ አሁን መጪውን የክረምት ወራት ግምት ውስጥ በማስገባት የዚህ ክትባት ዘመቻ በዚህ ክልል እንዲካሄድ ተደርጓል በማለት የገለጹ ሲሆን በሽታውን መከላከል የሚቻል ሲሆን ዋናው የንጸሁህ ውሃ አቅርቦትን ማመቻቸት እንደመሆኑ ይህም እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በስተመጨረሻም ሁሉም የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በደባርቅ ከተማ ቁልጭ ሜዳ በመባል በሚታወቀው ቦታ የሚገኘውን የስደተኞች ጣቢያ የጎበኙ ሲሆን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኘውን የጤና ጣቢያ፣ የስደተኞቹን መኖሪያ፣ የውሃ አቅርቦት ሁኔታ፣ ወዘተ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡