የኮሌራ ክትባት የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው
የኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችና የጤና ክስተት ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት በጋምቤላ፣በኦሮሚያ፣በደቡብ፣ በሶማሊያ እና በሲዳማ ክልሎች በኮሌራ የተጠቁ 20 ዞኖች እና 32 ወረዳዎች ሲሰጥ የነበረዉ የወረርኝ ምላሽ ስራዎች እና በሁለት ዙር ሲሰጥ የነበረውን የኮሌራ ክትባት አፈጻጸም አስመልክቶ ከመጋቢት 10 እስከ 11/2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የግምገማ መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የመድረኩ ዋና አላማ በወረርሽኝ ምላሹ ተግባራቶች እና በክትባት ዘመቻው ወቅት የተገኙ ውጤታማ ስራዎችን እንዲሁም ታይተው የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ኮሌራን ለመከላከል በሚደረጉ የተለያዩ ስራዎች ላይ ግምገማ እና ምክከር ለማድረግ ነው፡፡
አቶ መስፍን ወሰን የኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችና የጤና ክስተት ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመድረኩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደ ገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ችግሮችን ለመፍታት በተለይም የኮሌራ ወረርሺኝን በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ብሎም ለማጥፈት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን፣ ከነዚህ ስራዎች መካከል በሽታውን ለመግታት የኮሌራ ወረርሽኝ መከላከል እና የክትባት ዘመቻ አንዱ መሆኑን እና ወረርሽኙ ከተከሰተባቸዉ ወረዳዎች መካከል ከ95 ፐርሰንት በላይ ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ በዘላቂነት ወረርሽኙን ለመከላከል አለምቀፍ ኮሌራን የማጥፋት ግብረ-ሃይል ያሰቀመጠውን መመሪያ መሰረት በማድረግ እስትራቴጂክ አቅጣጫ መዘጋጀት መቻሉንና በቀጣይም ኮሌራን ለመከላከል የሚያገለግል የ10 ዓመታት እቅድ ተዘጋጅቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ኮሌራ ወረርሺኝ በአብዛኛው የሚከሰተው የአካባቢ እና የግል ንጽህና እጥረት እንዲሁም የግንዛቤ እጥረት ባለባቸው በታዎች ስለሆነ የችግሮቹ ምክንያቶች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ መስፍን ወሰን በመጨረሻ ማሳሰቢ ሰጥተዋል፡፡
ደ/ር ሞቲ ኢዶሳ የኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችና የጤና ክስተት ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት የባክቴሪያል በሽታዎች ቅንት እና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ በበኩላቸው የኮሌራ ወረርሺኝ ተከስቶ በነበረባቸው ቦታዎች ለሁለት ዙር ሲሰጥ የነበረው ክትባት በሽታውን ከመግታት አንጻር ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጃ በኮሌራ ሊጠቁ የሚችሉ 118 ወረዳዎች መለየታቸውን እና በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ክትባትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በወረርሽኙ ምላሽ ወቅት ሲሳተፉ፣ ሲያስተባብሩ እና ሲመሩ የነበሩ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ሃላፊዎች እንዲሁም ተወካዮች በመድረኩ ላይ እየተሳተፉ ከመሆኑም በላይ የአፈጻጸም ሪፖርት ከየወረዳዎች እየቀረቡ ሲሆን ግምገማና የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጠባቸው ይገኛል፡፡