የኮሮና ቫይረስ መረጃ
አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት እንደቀጠለ ነው፡፡ እስከ ጥር 22, 2020 ባለን መረጃ መሰረት በአጠቃላይ 9,826 ህሙማን ሲኖሩ ከነዚህም 213 ታካሚዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 245 ታካሚዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፡፡ ቻይና፤ የቫይረሱ መነሻነት 9,720 ታካሚዎች ሲኖሯት ሁሉም የሞት ቁጥር ሪፖርት የተደረገባትም አገር ናት፡፡ ከቻይና ውጪ 19 አገራት በአጠቃላይ 106 በቫይረሱ የተጠቁ ታካሚዎች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ጀርመን፤ አሜሪካ፤ አውስትራሊያ፤ ሲንጋፖር፤ ሩሲያ፤ ካናዳ፤ ህንደ፤ ዩናይትድ አረብ፤ ታይላንድ እና ጃፓን በተለያየ መጠን የበሽታውን መገኘት ሪፖርት አርገዋል፡፡ ከዚህም በፊት ይፋ እንደተደረገው በሀገራችን በቫይረሱ የተጠረጠሩ 4 ታካሚዎች ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ በተደረገው ምርመራ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ወደ ሀገራችን በሽታው እንዳይገባ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፤ በዚህም ዋናው እና ከፍተኛ ድርሻ ሚይዘው በቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በቫይረሱ የሚጠረጠሩ ሰዎችን መለየት ነው፡፡ እስካሁን ወደ 41,362 ተጓዦችን የማጣራት ምርመራ ተደርጎላቸዋል ከዚህም ውስጥ 1,251 ቫይረሱ ከተገኘባቸው አገራት የመጡ መንገደኞች ናቸው፡፡ በተለይ ቫይረሱን ሪፖረት ወደ አደረጉ አገራት የሚወስዱ ጉዞዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እያሳሰብን ፤ በሽታውን አስምልክቶ ላላችሁ ማንኛውም ጥቆማ እና ተጨማሪ መረጃ ነጻ የስልክ መስመር 8335 እንዲጠቀሙ እና የበኩሎን እንዲወጡ እናሳስባልን፡፡
ምንጭ፡ የአለም የጤና ድርጅት ኮሮና ቫይረስ ሰቹዌሽናል ሪፖርት 11