የኮቪድ በሽታ ለመከላከል ጥናትና ምርምር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
የኮቪድ በሽታ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጥናትና ምርምር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ COVID 19 NATIONAL COHORT STUDY (CNCS) በሚል ርዕስ ለአንድ አመት የሚቆየውን የኮቪድ በሽታ የሚፈጥረውን የተለያየ የህመም ስሜትና ልዩ ልዩ ባህርያቶቹን፤ ከሥርዓተ ምግብ ጋር ያለውን መስተጋብር እንዲሁም በህክምና ማገገሚያ ውስጥ ቆይታ በነበራቸዉ ታካሚዎች ላይ ክትትልና ጥናት በማድረግ መፍትሄዎችን የሚያመላክት ጥናት በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የኮቪድ በሽታ ለመከላከል ለሚደረገው ጥናት የጤና ሚኒስትር የሚጠበቅበትን እገዛ እንደሚደርግ አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ኤባ አባተ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኮቪድ በሽታ ለመከላከል እንዲረዳ የሚከናወነው ይህ ሀገራችን በአይነቱ ልዩ የሆነውና ለአንድ አመት የሚቆየው ጥናት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ በማተኮር የሚያጠናው ሲሆን በጥናቱም ከ 20 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ በሀገር እና በውጭ ሀገር ያሉ ምሁራን የሚሳተፉበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የኮቪድ በሽታ ለመከላከል ቀዳሚው የህብረተሰቡ ቅድመ መከላከል ጥንቃቄዎች ትልቅ ቦታ ያላቸው በመሆኑ አሁንም ቢሆን ህብረተሰቡ ለአፍታም ቢሆን ሳይዘናጋ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንዲተገብር አሳሳበዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባልደረባ በሆኑት በዶ/ር ማስረሻ ተሰማ እና በወ/ሮ ሳሮ አብደላ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡