የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ የዝግጁነትና ምላሽ ስራዎችን የመሰነድ ሶስተኛ ዙር አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ የዝግጅትና ምላሽ ስራዎችን በዶክመንት የመሰነድ ስራ ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራርና ባለሙያዎች ጋር ከህዳር 5 እስከ 9/2016 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ሶስተኛ ዙር አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ዶ/ር መልካሙ ሐብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በዝግጁነት፣ በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል ያሉ በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን ያስተማረ በመሆኑ በዚህ አውደ ጥናት ላይ የነበሩ መልካም ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮቶች እና አጠቃለይ ቅንጅታዊ ስራዎች በመረጃ የሚሰንድበት በመሆኑ የተገኙ ልምዶችና እውቀቶችን የጋራ በማድረግ ውጤታማ ሰነድ የሚዘጋጅበት መድረክ ነው ሲሉ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከአለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ አቶ አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ከተከስተም በኋላ እንዲሁም መቆጣጠር አስከቻልንበት ጊዜ ያሉትን ፈታኝ ወቅቶች እንዴት ማጠናቀቅ እንደተቻለና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በአጠቃላይ የሁሉም በለድርሻ አካላት አስደናቂና አስገራሚ ቅንጅት ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ ለአለም የምናጋራው አንድ ወጥ የሆነ ዶክምንት ለማዘጋጀት በመገናኘታችን እጅግ አስደሳች ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም ዶክምንቱ እስኪጠናቀቅ አብረን የምንሰራ መሆኑን አረጋግጣለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ ኮቪድ-19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ ስራዎችን በመረጃ በመያዝ፣ መልካም ተሞክሮዎች፣ ልምዶችና እውቀቶች የተቀመሩ እና ከሌሎች አገሮች የተወሰዱ ተሞክሮዎች እና ሃገራችን ለሌሎች ሃገራት ያካፈለቻቸውን ልምዶች የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወረርሽኞች የቅድመ ዝግጅትና ምላሽ ስራዎች በአንደኛና ሁለተኛ ዙር የተዘጋጁ መረጃዎች በጽሁፍ ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን አቶ ሙሉቀን ሞገስ የኢንስቲትዩቱ የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች፣ የክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የተለያዩ የአጋር ድርጅት ተወካዮች በአውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡