የኮቪድ-19 ወቅታዊ መረጃን በተመለከተ በየኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመገናኛ ብዙሃን የተሰጠ ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም፣አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ
የኮቪድ-19 ስርጭት በሃገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሚባል የህብረተሰብ ክፍል በበሽታው የተያዙ ከመሆኑም በላይ በቫይረሱ የሚያዙና ወደ ፅኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ እንደዚሁም ሕይዎታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበሩት ሳምንታት እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ወረርሽኙ ለረዥም ወራት ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ መሰላቸት ምክንያት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው የመከላከያ መንገዶችን የመተግበር እንዲሁም የመከላከያ ክትባት ለመውሰድ የታየው ዳተኝነት አሁንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አስደንጋጭ አድርጎታል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጥቅምት 1 እስከ 7 /2014 ዓ.ም ከተመረመሩት 52,424 ሰዎች መካከል 4,771 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የመያዝ ምጣኔም 9 በመቶ ሆኗል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ 227 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህይዎታቸውን ያጡ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 98፣ በኦሮሚያ ክልል 70፣ በአማራ ክልል 8፣ በሲዳማ ክልል 8፣ በደቡብ ክክልል 10፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር 10 ፣ በሶማሌ ክልል 20፣ በሃረሪ ክልል 2 እና በቢንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 1 ሰዎች ህይዎታቸው ማለፉ ተመዝግቧል፡፡
በአሁኑ ጊዜ 1,202 ሰዎች በህክምና ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም መካከል 600 የሚሆኑት ታካሚዎች ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል ገብተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡
ይህም በሀገራችን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የበሽታው ስርጭት መኖሩንና አሁንም የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን አዘውትሮ መተግበርና እንዲሁም የመከላከያ ክትባቱን ሳይዘገዩ መውሰድ ሊከሰት የሚችለውን የሕመም ስቃይን እና ሞትን መከላከል እንደሚገባ ያሳያል፡፡ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን ሲባል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ እጅ መታጠብና ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም ክትባቱን መውሰድ ላይ የሕብረተሰቡ ቁርጠኝነት ያነሰ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢና ውስብስብ አድርጎታል፡፡
በመሆኑም በተደጋጋሚ ጊዜ ለመግለጽና ለማስታወቅ እንደተሞከረነው አሁንም የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ማህበራዊ፣ኦኮኖሚያዊ እና ሰባዊ ቀውስ ለማስቆም የሚከተሉትን የመከላከያ ዘዴዎችን ሁላችንም ልዩ ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ ማድረግ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም
- መመሪያ 803/2013 ዓ/ም ተግባራዊነት ላይ በየደረጃው የሚገኝ ኃላፊነት የተጣለበት ግብረ-ኃይል (አመራርሮች፣ የጸጥታ አካላት እና ማህበረሰቡ) ትኩረት መስጠት
- በየደረጃው የሚገኝ አመራር በኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ትግበራ ላይ ለማኅበረሰቡ አርዓያ መሆን
- ሚዲያዎች ተገቢውን የአየር ሰዓት በመስጠት ለሕብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ማድረስ
- በህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት የሚፈጠሩ መሰባሰቦችን ማስቀረት
- የመንግስት፣ የህዝብ እና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ ማድረግ
- የኮቪድ-19 ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አፋጣኝ ምርመራ ማድረግ
- ሁሉም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነው የማህበረሰብ ክፍል የኮቪድ-19 ክትባትን በመንግስት ጤና ተቋማት በመሄድ መውሰድ
- ት/ቤቶች በመከፍት ላይ በመሆናቸው ሁሉም ት/ቤቶች የኮቪድ መከላከያ መንገዶች መተግበራቸውን መከታተል ይገባቸዋል፡፡ለዚህም አስተማሪዎች፣ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ኮቪድ-19ን በጋራ እንከላከል!