የዓለምአቀፍ የጤና ደንቦች (2005) የአቅም ግምገማ ተካሄደ

በሀገር ደረጃ እያንዳንዱ የWHO አባል ሀገር የሚያከናውነው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ አቅም ግምገማ ወርክሾፕ በአዳማ ከተማ ከህዳር 29 – ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያለችበትን ደረጃ በመገምገም ለዓለም ጤና ጉባኤ ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊ ከመሆኑ አንፃር ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በዚህ ዙሪያ በተዘጋጀው ወርክሾፕ ላይ ጥሪ ተደርጎላቸው 50 ያህል አባላት ተሳትፈዋል፡፡
ይኸንን ሀገራዊ ፋይዳ ያለውን ዓመታዊ የጤና ግምገማ ወርክሾፕ በንግግር የከፈቱት አቶ አስቻለው አባይነህ የአ.ህ.ጤ.ኢ. ም/ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ የዓለም ጤና ደንቦችን መርህ በተከተለ መንፈስ በአግባቡ ተገምግሞ ሀገራችን ያለችበትን ደረጃ አመላካች ሪፖርት እንደሚዘጋጅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ዶ/ር ፈይሣ ረጋሣ የወርክሾፑ አስተባባሪ የአባል ሀገራት ዓመታዊ የግምገማ ሪፖርት (SPAR) አስፈላጊነትና ዋና ዋና ዓላማዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን አቶ ሻምበል ሐበቤ በበኩላቸው ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተሰጠውን ምላሽና የተገኘውን ትምህርት አስመልክተው ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡ በቀረቡት ሁለቱም ጽሁፎች ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰንዝረው ተስተናግደዋል፡፡
ዶ/ር ማርቲን ሊቪነስ ከ WHO የዓባላት ሀገሮች ዓመታዊ ሪፖርት የመገምገሚያ ነጥቦችን አሰራር በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ከየዘርፉ ተወክለው የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በ3 ቡድን ተከፋፍለውና የመገምገሚያ ነጥቦችን መሠረት አድርገው የተዘጋጀውን የመገምገሚያ ፎርም በጥንቃቄ ሞልተዋል፡፡
እያንዳንዱ ቡድን የመከረበትንና የደረሰበትን የግምገማ ውጤት ለተሳታፊዎች አቅርቦ ሰፊ ሙያዊ ክርክርና ውይይት ከተደረገበት በኋላ የጋራ መግባባት ላይ በተደረሰው መሠረት የተዘጋጀው የመመዘኛ ፎርም ተሞልቶ ወርክሾፑ ተጠናቋል፡፡