የዓለም ዓቀፍ የጤና ደንብ አተገባበር የአቅም ግንባታ ሪፖርት አውደ ጥናት ተካሄደ
የኢንስቲትዩቱ የዓለም ዓቀፍ የጤና ደንብ አተገባበር የአቅም ግንባታ ሪፖርት ለማዘጋጀት የተለያዩ ተጠሪ መስሪያ ቤት ተወካዮች በተኙበት ከህዳር 15 እስከ 17/2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ ላይ ተገኝተው እንደ ገለጹት እንደ ሃገር የተገባውን ቃል ኪዳን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ተልዕኳችንም ህይወትን ማዳን ነው፤ነገር ግን ካለፈው ዓመት ጀምሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሁሉም ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ልናሳካቸው ያቀድናቸውን ስራዎች እንዳንሰራ ከማድረጉም በላይ አሁን ሃገራችን ያለችበት የውስጥና የውጪ ጫናዎች በጤናው ዘርፍ መድረስ የሚገባን ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት ሊፍጥር ቢችልም ባደረግነው ቅንጃታዊ ስራ ወደኋላ አልተመለስንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው በሁሉም ተቋማት የተሰሩ ስራዎችን በመገምገምና በመፈተሸ ክፍተት የታየባቸውን ጉዳዮች ምን ብናደርግ በተሻለ መንገድ ልንፈታቸው እንችላለን የሚሉትን በመወያየት እና የጋራ እቅድ በማውጣት ወደስራ መግባት ያስፈልጋል፡፡እንዲሁም በሃገራችን ላይ የተደቀነውን የውጭና የሃገር ውስጥ ጫና ውጤታማ ስራ በማስመዝገብ ማሸነፍ እንደሚገባ በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ የአለም አቀፍ የጤና ደንብ የኢትዮጵያ ተጠሪ በበኩላቸው 196 ፈራሚ አገሮች ለአለም አቀፍ ጤና ድርጅት ጉባኤ የደንቡን አተገባበር የአቅም ግንባታ ሪፖርት ማቅረብ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ምክንያት የሃገራችንን ሪፖርት ለመላክ ከ15 በላይ የሚሆኑ ተጠሪ መስሪያ ቤቶች በአውደ ጥናቱ ላይ መሳተፋቸውንና ሪፖርቱ በባለሙያ ደረጃ መዘጋጀቱንና በቀጣይ በከፍተኛ አመራሩ ታይቶ ከጸደቀ በኋላ የሚላክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአለም አቀፍ መስፈርት መሰረት በአለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ የ2014 ዓ.ም ሪፖርት ሳይጨምር የተካታታይ የ3 ዓመታት ሪፖርት ከአማካይ ውጤት በላይ መሆኑን ገልጸው ውጤቱም በሃገር ደረጃ የተሻለ ስራ መሰራት እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆኑን ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ሰፊ ግምገማና ውይይት ከመደረጉም በላይ በአለም አቀፍ የጤና ደንብ የአቅም ግንባታ መስፈርት መሰረት የሃገሪቱ የጤና ደረጃ በምን ላይ እንደሚገኝ በቀረቡት የአለም አቀፍ የጤና ደንብ መጠይቆች በአወደ ጥናቱ ተሳታፊ በነበሩ የተጠሪ መስሪያ ቤት ባለሙያዎች የተሞሉ ሲሆን የግምግማ ሪፖርቱ በከፍተኛ አመራሩ ታይቶ ከጸደቀ ባኋላ ለአለም ጤና ድርጅት ጉባኤ የሚላክ ይሆናል፡፡