የጊኒዎርም በሽታን ተባብረን እናጥፋ
28ተኛዉ አገር አቀፍ የጊኒዎርም በሽታ ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የካርተር ሴንትር፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የክልሎች ጤና ቢሮ እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት ከ19-20/2016 ዓ.ም ተካሄደ።
ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በዓመቱ ዉስጥ የተከናወኑ በርካታ ሥራዎች አፈጻጸም የሚቀርብበት፣ የሚገመገምበት እንዲሁም ዉይይት የሚካሄድበት እና በቀጣይ ትኩረት የሚሰጥባቸዉ ጉዳዮች ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት 28ኛዉ በአቡዳቢ ላይ በተደረገዉ የጤና ጉባዔ መጨረሻም በሽታዉን ከቀሪዉ አለም አገራት ዳግም እንዳይታይ ለማጥፋት ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል፡፡ በጉባዔዉም በአለም ደረጃ የተለየ አካሄድ እና ቁርጠኛነት መታከል እንዳለበት ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን እኛም በ27ኛዉ አመታዊ ጉባዔ ከወትሮ የተለየ ርቀት መሄድ እንደሚገባን አቅጣጫ ማስቀመጣችን ይታወሳል፡፡ ካርተር ሴንተር እና የአለም የጤና ድርጅት ረጅም ቆይታ ጊዜ ያላቸው ፕሮግራም ፈጻሚ አካላት ሲሆኑ ሁሉንም የመንግስት መዋቅር ያሳተፈ፤ ባለቤትነትን ያረጋገጠ፤ ሕብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ የሆነ የአፈጻፀም ስርዓት መከተል እንዲቻል ምክክር ማድረጋችንም ይታወሳል፡፡ ይህም ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ተቀራርቦ መስራት፤ድጋፋዊ ክትትል ማድረግ፤አፈጻፀምን መገምገም፤ክፍተቶችን ለመሙላት በጋራ ማቀድ እና የመሳሰሉ ስራዎች መሻሻል ማሳየታቸዉ እንደመልካም ስኬት አይተናል በማለት ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ አያይዘዉም ይህ ጉባዔ እስካሁን የነበሩንን አገር አቀፍ እና የአህጉሩን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ በመዉሰድ፤አለም አቀፍ ዉሳኔዎችንና ድንጋጌዎችን እንደመርህ በመከተል በቀጣይ ዓመታት የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ እና አገራችንም በሽታዉን ፈጽሞ የምታጠፋበት ጊዜ እንዲሆንና መልካም የውይይት መድረክ እንዲሆን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት የጊኒዎርም በሽታን ለማጥፋት በርካታ ስራዎች መሰራታቸው በ2015 ዓ/ም በሽታውን ለመከላከል በተደጋጋሚ በሽታው የሚታይባቸውን አካባቢዎች የንፁህ የመጠጥ ውሀ ተደራሽ መደረጉን፣ በክልሉ ያሉ ኩሬዎች ላይ የክትትል ስራ መሰራቱን፣ የበሽታው ስርጭት የታየባቸው አካባቢዎች ላይ የእንሰሳት እንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን እንዲሁም በርካታ የተሰሩ ስራዎችን የጠቀሱ ሲሆን በዚህም ምክንያት የጊኒዎርም በሽታ ከአገራችን ጨርሶ ለማጥፋት ጫፍ ላይ መደረሱ ተቁመዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ አያይዘዉ በሀገራችንም በሽታዉ እ ኤ አ በ2023 በሰዉ ላይ አለመከሰቱ ጥሩ ጅምር መሆኑን አንስተዉ ከእንስሳት ጋር በተያያዘ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር በሽታዉ በእጅጉ ቀንሶ ቢታይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት የአፍሪካ አገራት ላይ በሸታዉን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አልተቻለም ስለሆነም በሚፈለገው ደረጃ በሽታውን ከምንጩ ለማድረቅ እዚህ የተገኘን አካላት በቅንጅት በመስራት የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል በማለት ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጋምቤላ ሕ/ክ/መ/ርዕሰ-መስተዳድር ተወካይ አቶ ፒተር አማን እንደገለፁት የጊኒዎርም በሽታን ከሀገራችን ለማጥፋት ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት በተደረገዉ ሰፊ እንቅስቃሴ ስርጭቱን ለመግታት ከመቻሉም በላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ማጥፍት ደረጃ የተደረሰበት ዉጤት ማስመዝገብ ቢቻልም ከሁለት ዓመታት በፊት በ2013 እና በ2014 ዓ/ም በተለይ በክልሉ ከሰዉ ልጅ አልፎ በቤት እንስሳት እና በዝንጀሮ መከሰቱን ገልፀዋል።
አክለውም ከዚህ አንፃር ዛሬ የሚጀመረዉና ለሁለት ቀናት የሚካሄደዉ 28ኛዉ አመታዊ የጊኒ ወርም መከላከል ዕቅድ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ ዋና አላማ የእቅድ አፈፃፀማችንን በመገምገም ተጠናክረዉ መቀጠል የሚገባቸዉን ጠንካራ ተሞክሮዎች እና በአፈፃፀም ሂደት የታዩና መሻሻል የሚገባቸዉ ክፍተቶች በመለየት በቀጣዩ አመት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተዉ በመንቀሳቀስ የጊኒዎርም በሽታን ከክልሎች ብሎም ከሀገራችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፍት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይም ዶ/ር ፖዉል ሜኑካ በአለም የጤና ድርጅት የበሽታ መከላከል መሪ ተወካይ እንዲሁም አቶ አዳም ዋይስ፡ ካርተር ሴንተር አትላንታ የጊኒ ዎርም ፕሮግራም ዳይሬክተር ንግግር በማድረግ ለፕሮግራሙ ስኬት ያላቸውን የአጋርነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡