የጊኒዎርም የማጥፋት ፕሮግራምን አስመልክቶ የተካሄደው የምክክር አውደጥናት ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ የጊኒዎርም የማጥፋት ፕሮግራምን አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከህደር 16 እስከ 17/2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በኤክስኩቲቭ ሆቴል የተካሄደው የምክክር አውደ ጥናት ተጠናቀቀ፡፡
የምክክር አውደ ጥናቱ ዓላማ የጊኒዎርም የማጥፋት ፕሮግራም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች፣በሽታውን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት እሰካሁን የተሄደባቸውን በማጠናከር ብሎም አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦችን በመፍጠር ክፍተቶችን በተሻለ ለመቅረፍ እና በቀጣይ የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደ ተናገሩት የጊኒዎርም በሽታን ከሃገራችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን እና ከፍተኛ የሆነ ውጤት መመዝገቡን፣ነገር ግን ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አንስቶ እስከ አሁን በሽታው በ11 ሰዎች ላይ እና በ15 እንስሳት ላይ መገኘቱ፣ በሽታውን ለማጥፋት የተደረገውን ጥረት ወደኋላ እንዳይመልሰው ስጋት የፈጠረ መሆኑን እንዲሁም ችግሩን በተገቢው መንገድ ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ የሆነ ቅንጅት እና ርብርብ የሚጠይቅ ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጊኒዎርም በሽታ የመከላከያ ክትባት የሌለው ከመሆኑም በላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች የሚፈጠር እና በእንሰሳትና በሰው ላይ መገኘቱ ችግሩ በፍጥነት እንዳይወገድ አድርጎታል፤ ስለዚህ የብዙ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልገዋል ሲሉ ሚኒስትሯ አያይዘው አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ኤባ አባተ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የጊኒዎርም በሽታ ከሌሎች በሽታዎች የሚለየው ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ማወቅ የሚቻለው ከዓመት በኋላ ነው፤ይህ ደግሞ በሽታውን በቀላሉ ለማጥፋት አስቸጋሪ አድርጎታል፤ ስለዚህ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ማንኛውም የመንግስት ሃላፊነት የተቀበለ አካል ሁሉ በሽታውን ለማጥፋት መሰለፍ አለበት፤በመሆኑም ይህ የምክክር መድረክ በምን መንገድ ስራችንን ብንሰራ ነው ችግሩን መቅረፍ የምንችለው የሚለውን በመወያየት መግባባት ላይ ለመድረስ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
በተደረገው የሁለት ቀን የምክክር አውደጥናት በሽታዉን ለማጥፋት እስካሁን እየተሄደባቸዉ ባሉ ስራዎች እና ተግዳሮቶች ላይ ሰፊ ዉይይት የተደረገ እና የመፍትሔ ሀሰቦችም የተቀመጡ ሲሆን የታዩ ተግዳሮቶችን መሠረት በማድረግ፣ የተለያዩ ጉዳዮችን በመዳሰስ ፣ በሽታዉን ለማጥፋት የሚረዱ ተግባራትን በመለየት እና የድረጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት እንዲሁም ከሚመለከታቸዉ ተቋማት እና ሌሎች አካላት ጋር የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ በኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ የማጠቃለያ ሀሳብ እና አቅጣጫ ተሰጥቶ የምክክር አዉደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እና የኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ሃላፊዎች፣የጋምቤላ ክልል የቢሮ ሃላፊዎችና አመራሮች ፣የአለም ጤና ድርጅት እና የካርተር ሴንተር ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች በምክክር አውደ ጥናቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡