የጊኒ ወርም በሽታን ለማጥፋት የሁሉንም አካላት ትኩረት ይሻል
ጋምቤላ ታህሳስ 5/2009 የጊኒ ወርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየተካሄደ ላለው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ሜድ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን አስታወቁ።
የጊኒ ወርም በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉትን ስራዎች የሚገመግመው 21ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው ።
የዓለም ሎሬትና የአፍሪካ የጊኒ ወርም ማጥፋት ፕሮግራም የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በግምገማው ላይ እንደገለጹት በሽታውን ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት የሁሉንም አካላት ትብብርና ትኩረት ይሻል።
በመሆኑም የድህነት መገለጫ የሆነውን የጊኒ ወርም በሽታ በመግታት ሀገሪቱን ከበሽታው ነፃ ለማደረግ ከሀገር አቀፍ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብርና በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የበሽታው ስርጭት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ ሀገራት ብቻ እንደሚገኝ ገልጸው በሽታውን በማጥፋት ረገድ ከሌሎቹ ወደ ኋላ ላለመቅረት በርትቶ መስራት እደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ዶክተር አማሃ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሽታውን ለማጥፋት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች የስርጭት መጠኑን ለመቀነስ ተችሏል።
” በፈረንጆች የዘመን አቆጣጠር በ1994 በኢትዮጵያ የጊኒ ወርምን የማጥፋት ዘመቻ ሲጀመር በበሽታው የተጠቁት ሰዎች ቁጥር አንድ ሺህ 252 የነበረው በ2016 ወደ ሶስት ዝቅ ማደረግ ተችሏል” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የበሽታው ስርጭት በሀገሪቱ ሌሎች አከባቢዎች ጠፍቶ በጋምቤላ ክልል ጎግ ወረዳ ብቻ እንደሚገኝም ዋና ዳሬክተሩ ጠቁመዋል።
“በሽታው የመተላለፊያ መንገዱ ባልተወቀ ምክንያት በእንሰሳት ላይ መታየቱ በሽታውን ለማጥፋት እየተከናወኑ ባሉት ስራዎች ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል “ብለዋል።
ይሁን እንጂ ኢንስቲትዩቱ የተጠናከረ የቅኝትና የህዝብ ንቅናቄ ስራዎችን በማከናወን በመጪው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ የበሽታውን ስርጭት ሙሉ ለሙሉ ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የካርተር ማዕከል የጤና ፕሮግራም ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክትር ዲን ሲንኮ በዚሁ ጊዜ እንደገጹት በዓለም ላይ የጊኒ ወርም በሽታ ማጥፊያ ፕሮግራም ማጠቃለያ ደረጃ ላይ ቢደረስም የመጨረሻው አካባቢ ፈታኝ እየሆነ ነው።
”ባለፈው ዓመት በዓለም በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 22 ብቻ ነበር፣ በዚህ ዓመት ግን ከዚያ በላይ ሆኗል፤ ይህ የሆነው ደግሞ በቻድ የታየው ክስተት ነው፤ በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የበሽታውን ስርጭት በመቀነስ ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ” ብለዋል።
“ማዕከሉ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት አዲስ የጊኒ ወርም በሽታ ክስተት እንዳይኖር ይፈልጋል” ያሉት ዶክተር ዲን ለስኬታማናቱም ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል ።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በበኩላቸው የበሽታውን ስርጭት ለማጠፋት ሰፊ ስራዎች ቢከናወኑም ከህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስና የውሃ አጠቃቃም ችግር ጋር ተያይዞ ሒደቱ ጊዜ ወስዷል ብለዋል።
በሽታው በሃገራችን በተለይ በጋምቤላ ክልል ሲገኝ እንደነበረ ርዕሰ-መስተዳደሩ ገልጸው መንግስት በሽታውን ከክልሉ ለማጥፋት የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የመስክ ምልከታ በማድረግ ትናንት በጋምቤላ ከተማ በተጀመረው ዓመታዊ የጊኒ ወርም ግምገማ ላይ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የአመራር አካላትና ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በፈረንጆቹ 1986 በዓለም የጊኒ ወርም በሽታን የማጥፋት መረሃ-ግብር ሲጀመር በአፍሪካና በኤሲያ በሚገኙ 20 ሀገራት ሶስት ነጠብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በበሽታው ይጠቃ እንደነበር የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ