የጤናዉ ስርዓት ለማዘመን ጥራት ያለዉ የጤና መረጃ አስፈላጊ መሆኑ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ጥራት ያለዉ መረጃ በማደራጀት የስርዓተ ጤናዉን ወደ ተሻለ እርከን ለማሻገር የሚቻልበት ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት የጥራት ማስረጃዎች ለጤና ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ኔትወርክ (QuEST) ልኬትን በማሻሻል፣ መፍትሄዎችን በመሞከር እና አጠቃላይ እውቀትን በመፍጠር እና ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ካሉ ለውጥ ፈጣሪዎች ጋር በመተባበር ወደ ከፍተኛ ጥራት ያለው የጤና ስርዓት ለመሸጋገር የሚያስችል የማስረጃ መሰረት ለመገንባት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራር ለፕሮጀክቱ ስኬታማ እና ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና የፕሮጀክቱን ግኝቶች ወደ ሕብረተሰብ ጤና አሠራሮች እና ከዚያም በላይ እስኪተረጎም ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ክትትልና እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዉ ለዚህ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እና በዚህ ጥናት ውስጥ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
የBMGF በኢትዮጵያ በተሰኘዉ ድርጅት የጤና እና ስነ−ምግብ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሚስስ ሱዛን በበኩላቸዉ ጥራት ያለዉ የጤና እንክብካቤ ለተገልጋዮች ማበርከት በጤና ስርዓት ዉስጥ ቁልፍ ቦታ እንዳለዉ ገልፀዉ፤የጤናዉን ስርዓት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ጥራት ያለዉ መረጃ መኖሩ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያብራሩ ሲሆን ይህም አሁን ያለዉን የጤና ስርዓት ክፈተቶች ጥንካሬ ለመመዘን እንዲሁም በተለያዩ የጤና አገልግሎት አሰጣጦች ላይ አዳዲስ አሰራሮች ለመዘርጋት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡