የጤና ስርዓቱን ለመደገፍ ሁሉን አቀፍ የተጠናከረ እቅድ መኖር ወሳኝ መሆኑ ተገለጠ
የጤና ስርዓቱን ወቅታዊና ታማኝ በሆነ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ለማገዝ እንዲቻልና ለችግሮች መፍትሔዎች ሰጭ ጥናቶችን በማካሄድ ለጤና ስርዓቱ በቂና ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ለማቅረብ ይቻል ዘንድ የተጠናከረ እቅድ መኖር አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ዶ/ር ጽጌሬዳ ክፍሌ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በዛሬው እለት በተጀመረው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከክልል የጤና ቢሮዎች ጋር በሚመክርበት የጋራ እቅድ ዝግጅት ስብሰባ ላይ በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ እንዳስገነዘቡት ውጤታማ መሆን የሚቻለው በጋራ መስራት ሲቻልና ያለውን ውስን ሀብት በጋራ መጠቀም ሲቻል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ በሽታን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ የሆኑ እንደ ኮሌራ፡ ቢጫ ወባ፡ ደንጉ ፌቨር እና ሌሎችም አደጋዎች የአገራች የጤና ስጋቶች በመሆን የቀጠሉ በመሆናቸው በአጽንኦትና በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተርዋ አስታውቀዋል፡፡
ዘመናዊ ህክምናን በሰለጠነ የሰው ሃይልና በዘመናዊ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች በማደራጀት ወረርሽኞችን በላቦራቶሪ በማረጋገጥ፣ የህክምና አገልግሎቱን ጥራት ባለው የላቦራቶሪ ምርመራ ለመደገፍ እንዲሁም ጥናትና ምርምሮችም በላቦራቶሪ የተደገፉ ለማድረግ የሁሉም ርብርብ የሚጠይቅና ያለውን ሀብት (የሰው፣ የገንዘብ እና የማቴሪያል) በጋራ በማቀናጀት እንደ ሀገር ውጤታማ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ጽጌሬዳ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን ከማዘጋጀት ባሻገር በየአካባቢው ቋንቋ በመተርጎም ለችግር መፍትሔዎች አድርጎ መጠቀም ስለሚቻልበት መንገድ፡ ለወረርሽኞች ቅድመ ዝግጅት በማድረግ፣ ቅኝትን በማጠናከር፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠትና አፋጣኝ ምላሽ መስጠትን በተመለከተ፤ ለኮቪድ 19 ሶስተኛ ዙር ማዕበል ምላሽ ትኩረት በመስጠትና ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ ማጠናከርን በተመለከተ፤ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች አስተዳደር ስርዓትን ማጠናከር ስራዎችን አስመልክቶ፡ የላቦራቶሪዎችን ጥራት መጨመር ትርጉም ባለው መልኩ ትራንፎርም በሚያደርግበት መልኩ የእቅዱ አካል ማድረግን በተመለከተ፤ የአዳዲስ ምርመራዎችን ማስፋፋት ስራዎችን በተመለከተ እንዲሁም በየጊዜው ወደ ክልሎች የሚላኩ በጀቶችን ቶሎ ማወራረድ አስመልክቶ እና ዲጂታላያዜሽን በተመለከተ በትኩረት የጋራ እቅዱ አካል እንዲሆኑና እንዲታዩ ዋና ዳይሬክተርዋ አሳስበዋል፡፡
በእለቱ በ2013 ዓ.ም የተከናወነው የተቀናጀ ድጋፋዊ ሱፐርቪዝን የተዘጋጀው ሪፖርት እና ለየክልሎች በየዓመቱ የሚላከው ፋይናንስ በተመለከተ በተገቢው ቦታና ጥቅም ላይ መዋሉና መወራረዱን በተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ውይይቶች ተካሂዶበታል፡፡