የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ፣ ዝግጁነት፣ ጥራት እና ተደራሽነትን አስመልክቶ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ይፋ ሆነ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤና እና ስነ- ተዋልዶ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዝግጁነት እና ጥራትን አስመልክቶ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ነሀሴ 11/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እስካይላይት ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡
የጥናቱ ዋና ዓላማ በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት የሚሰጡትን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እና ጥራት፣ የጤና ተቋማት ዝግጁነት፣ እና የተገልጋዮች እርካታን በተመለከተ ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ነው፡፡
ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የዓውደ ጥናቱን መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት በጤና ተቋማት የሚሰጡ በርካታ የጤና አገልግሎቶችን እና ተደራሽነታቸው ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያወቅንበትና በቀጣይ ተግባራዊ ለሚደረጉ ስራዎች ትኩረት በመስጠት እቅዶችን ለማዘጋጀት ትልቅ ግብዓት የሰጠ የዳሰሳ ጥናት ነው ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ከመሆኑም በላይ ጥናቱ ለሁለተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የተከናወነ መሆኑን በማንሳት በዚህ ጥናት በተለያየ ምክንያት ያልተካተቱ ቦታዎች በቀጣይነት ለማካተት እየተሰራ መሆኑን አንስተው አጠቃላይ ጥናቱ ለሁለት ዓመት የቆየ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን የዳሰሰ ጥናት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጥናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የ1158 የጤና ተቋማት ላይ የተካሄደ ሲሆን 32 የሪፈራል ሆስፒታሎችን፣ 123 አጠቃላይ ሆስፒታሎችን፣ 218 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን፣ 268 ጤና ጣቢያዎችን፣257 ጤና ኬላዎችን፣ 18 ከፍተኛ ኪኒሊኮችን፣139 መከከለኛ ክሊኒኮችን ፣103 መለስተኛ ክሊኒኮችን በአጠቃላይ 829 የመንግስት እና 329 የግል ጤና ተቋማትን ትኩረት አድርጎ የተሰራ ጥናት ነው፡፡
የጥናቱ ውጤትም እንደሚያመለክተው በጤና ተቋማት 92 በመቶ የህጻናት ጤና አገልግሎት፣ 84 በመቶ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አገልግሎት፣ 83 በመቶ የወባ ምርመራ ህክምና፣ 65 በመቶ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ 65 በመቶ የኤች አይቪ ምርመራ አገልግሎት፣ 64 በመቶ የቲቢ ምርመራ አገልግሎት፣ 54 በመቶ የእናቶች የወሊድ አገልግሎት፣ 51 በመቶ የህጻናት እድገት ክትትል አገልግሎት፣ 47 በመቶ የህጻናት ክትባትና 18 በመቶ የእድሜ ማራዘሚያ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ዝግጁነት፣ ጥራት እና ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከማሳየቱም በላይ በጤና ተቋማት ያሉትን ክፍተቶች በማሳየት በቀጣይ ሊተገበሩ የሚችሉ እስትራቴጂዎች፣ ፐሮግራሞች እና እቅዶች ለማዘጋጀት እንደግብአት እንደሚያገለግል ከቀረበው ጥናት መረዳት ተችሏል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ የስራ ክፍል ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ የአጋር ድርጅት፣ የኢንስቲትዩቱ ማኔጅመንት አባላትና ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡