የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበት ተገለጸ
በኢትዬጵያ የጨቅላ ህፃናት ሞት መጠን ከ1ሺህ በህይወት ከሚወለዱት 33ቱ ለህልፈት ይዳረጋሉ ይህም በፈረንጆቹ በ2016 ከነበረው አሀዝ (29 ሞት/1ሺህ ህጻናት) ጭማሪ አሳይቷል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዪት ምርምር ትግበራ ዳይሬክቶሬት (Knowledge Translation Directorate) የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ያስችል ዘንድ ከ 28-29/08/13 ዓ.ም በቀረበዉ የፖሊሲ ብሪፍ (evidence brief for policy) በቢሾፍቱ ከተማ ዉይይት ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይም የፖርላማ አባላትና፤ ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድረሻ አካላት በተገኙበት ዉይይት (Policy Dialogue) ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም ጨቅላ ህፃናት መታፈን (Asphyxia)፣ ኢንፌክሽን እና ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህፃናት፣ ለጨቅላ ህፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያት ናቸው ተብለው ተለይተዋል። በተጨማሪም የቅድመ ወሊድ ክትትል አለማድረግ ፣ በጤና ተቋማት አለመውለድ ቢወለዱም በቂ እና ጥራት ያለው አገልግሎት አለማግኘት፣ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው ተብለው ተነስተዋል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምር ትግበራ ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ት ፊርማዬ እንደገለጹት የምክክሩ ዋነኛ ዓላማ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ በመረጃ መደገፍና ብሄራዊ የጨቅላ ህጻናትና ልጆች ስትራቴጂ (national newborn and child survival strategy) ግብአት እንዲሆን ማድረግ ነዉ፡፡
በተጨማሪም ባለፉት 10 አመታት የእናቶች ሞትን መቀነስ ቢቻልም፣ የጨቅላ ህጻናትን ሞት መቀነስ ባለመቻሉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመው፤ ለዚህም የተለያዮ የመፍትሄ ሀሳቦች የተለዩ ሲሆን ማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎትን ማጠናከርና ተያያዥነት ባለው መልኩ ከቅድመ እርግዝና ጀምሮ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን የጤና አገልግሎት ማጠናከርና በየደረጃው ለሚሰጠው አገልግሎት የጥራት ደረጃ ማስቀመጥ ፣ ከግብአት አቅርቦት እና መሰረተ ልማት ጋር የተገናኙ ችግሮችን መፍታት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል።