ድርቅ፣ ከግጭትና ከወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ምላሽ መስጠትንና በጦርነት የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ ከአጋርና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ከድርቅ፣ ከግጭትና ከወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ የጤና ችግሮችን ምላሽ መስጠትንና በጦርነት የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ ከአጋርና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ በሸራተን አዲስ አካሄደ።
በምክክር መድረኩ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ፣ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ፣ የአጋር ድርጅቶች የስራ ሃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ከዚህ ቀደም ሲካሄዱ ከነበሩት መድረኮች ሰፋ ባለ መልኩ በርካታ አጋር አካላትና ለጋሽ ድርጅቶች የተሳተፉበት ሲሆን ስለ ድንገተኛ ወረርሽኝ፣ ከድርቅ፣ ከግጭት ጋር የተያያዘ የሰብአዊ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋምን፣ ስነ-ምግብን፣ የግልና የአካባቢ ንጽህናንና ጤናን የተመለከቱ የመነሻ ጽሁፍ ቀርበው ውይይት ተደርገውባቸዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ ጋር በመሆን ውይይቱን የመሩት ሲሆን፣ ከግጭት ጋር ተያያይዞ የተጎዱ አካባቢዎችን ማለትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር ፣ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችንና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ እንደ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ወባ፣ ሊሽማኒያሲስ እና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ቢሆንም አሁንም ትልቅ ትኩረት የሚሹ በመሆናቸው ሁሉም አጋር አካላት በትብብርና በቅንጅት ድጋፋቸዉን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ተደራራቢ የህብረተሰብ ጤና ችግር ሰፊ ምላሽ እንደሚያስፈልገው የገለጹት ዶ/ር ሊያ ታደሠ በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ የሆኑ አጋር አካላት ድጋፍ የሚሰጡ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ድጋፍ የሚሰጡ አጋር አካላት በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው ይህንን ማሻሻል እንደሚገባና የሚመጡ ግብዓቶችንና ድጋፎችንም በአግባቡ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የሚደርሱበትንና ክትትል የሚደረግበትን የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው በሃገሪቱ ከግጭቱ ጋር ተያይዞም ሆነ በድርቅ ምክንያት የሚከሰቱ የስነ-ምግብና የጤና ችግሮችን አስመልክቶ ምላሽ ለመስጠት በቅድመ ማስጠንቀቂ የቅኝት የመረጃ ስርዓት አማካኝነት የማጣራት ስራ እየተሰራ ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረው አሁን ካለው ዘርፈ ብዙ ችግር ጋር ተያይዞ አጋር አካላት ከጤና ሚኒስቴርና በየደረጃው ካሉ የጤና መዋቅሮች ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና የሚወጡበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን ብለዋል፡፡
በቅንጅታዊ ስራዎችም የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ፣ የሃብት አጠቃቀምንና ስርጭትን ፍትሃዊ እንዲሆን በማድረግ ምላሽ አሰጣጡን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ እንደተገለጸው በቀጣይ የአራት ወር የጋራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በሃገር አቀፍ ደረጃ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለሚመራው ካውንስል የሚቀርብ ሆኖ ከሌሎች ሴክተሮች ጋር በመቀናጀት በሃገር አቀፍ ደረጃ ለአሁን ብቻም ሳይሆን በረዥም ጊዜ ችግሮቹ እንዳይከሰቱ፤ ሲከሰቱም ፈጣን የሆነ ምላሽ ለመስጠት ዕቅዱ እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
በምክክር መድረኩ ማጠቃላያ ላይ በቅንጅታዊ አሰራር፣ በግብዓት አቅርቦትና ስርጭት፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅኝት ስርዓት፣ ከድንበር ተሻጋሪ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን በመቆጣጠር፣ በሃብት አጠቃቀም፣ በመረጃ ልውውጥ፣ በስነ-ምግብ፣ በውሃ እንዲሁም በግልና በአካባቢ ንጽህ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶችን መፍታት እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥና የአጋርና ለጋሽ ድርጅቶችን በማመስገን የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡