ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ለማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ’ በሚል መሪ ቃል የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ የመንግሰት ኃላፊዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄደ።
የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር የተከበሩ አቶ መስጠፌ ሙሐመድ ተሳታፊዎችን እንኳን ደህናመጣችሁ ካሉ በኋላ በክልሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት አንዱእንደሆነ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር የተከበሩ ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተከስቱትን እና ሊከሰቱ የሚችሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችንለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃዉ የምትገኙ ሚኒስትሮች ፣ ሚኒስቴር ድኤታዎች ፣ የክልል ፕሬዘንዳቶች ፣ የጤና ቢሮሃላፊዎች ፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሮች እና የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች አመራሮች በቅንጅትና በትብብርመስራት እጅግ አስፈላጊና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
አክለውም ሚኒሰቴሯ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአጭር ጊዜ አሁን የተከሰቱትንየሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች እና ወረርሺኞች ለመቆጣጠር የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ በዘመቻ መልክ ለመሥራት ቅድመዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል። ይህንንም እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በትብብር ለመከወን የሁላችሁንም አስተዋፅዖእንድታበረክቱ እያሳሰብኩ ለወደፊቱም ለምንገነባው የማይበገር የጤና ሥርዓት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ሥርዓትትልቅ አስተዋፅዖ ስላለው የበኩላችሁን ድጋፍ እና እገዛ እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉበበኩላቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮዽያ የተከሰቱ የተለያዩ ሰዉ ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ለተለያዩ ተላላፊበሽታዎች መከሰት እንዲሁም አጣዳፊ የምግቦች እጥረት መከሰት ምክንያት ሆነዋል። ”ይህ የንቅናቄ መድረክ እንደአከባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ያሉ ተግዳሮቶችን በሰፊው በመወያየት በከፍተኛ አመራሩ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረትበአጭር ጊዜ ውስጥ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይበልጥ በጋራ እና በተጠናከረ መልኩእንድንሰራ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፣’ ‘ በማለት ዶ/ር መሳይ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህናመጣችሁ መልዕክት ከማስተላለፋቸው በተጨማሪ በኢትዮዽያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ያለበትን ነባራዊሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ አቅርበው ወደፊት ምን መደረግ እንዳለበትና በጋራ እንዴት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በንቅናቄ መድረኩ በተላለፉ መልዕክቶች መሠረት የኮሌራ ወረርሽኝ በነሐሴ 21ቀን 2014ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሃረና ቡሉኮወረዳ ተከስቶ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችን አዳርሷል ።በሽታዉ ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ እስከ አሁን በአጠቃላይ 342 ወረዳዎችን ያዳረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በ255 ወረዳዎች ላይ በሽታዉን መቆጣጠር ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይበ9 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 87 ወረዳዎች ላይ በሽታዉ በወረርሽኝ መልክ እንደቀጠለ ይገኛል።
የኩፍኝ በሽታን በተመለከተ ወረርሺኙ ከተከሰተበት ነሀሴ 06/2015 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም 66,625 የኩፍኝታማሚዎች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣በአሁኑ ሰዓት በሽታዉ በ8 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በ101 ወረዳዎች በወረርሽኝ መልክእንደቀጠለ ይገኛል።
የወባ በሽታን በተመለከተ በሽታዉ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በወረርሽኝመልክ በሚባል ደረጃ የተከሰተ ሲሆን ፣ በሽታዉ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከጥር 1/2016 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም ድረስየታማሚዎች ቁጥርም 1,347,948 መሆኑን የቅኝት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ካለፉት 5 ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከተለመደው በተለየሁኔታ ከፍ ብሎ እንደነበር የቅኝት መረጃዎች ያመለክታሉ።
በመጨረሻም የፓናል እና አጠቃላይ ውይይት ተደርጎ ለወደፊት ትግበራ የሚረዱ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እናትግበራውን ለማሳካት ቃል በመግባት መድረኩ ተጠናቋል።