ጥራት ያለው መረጃ ለጤና ስርዓት ለውጥ ኔትዎርክ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በስረዓተ ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ጥራት ያለው መረጃ ለጤና ስርዓት ለውጥ (Quality Evidence for Health System Transformation(QuEST) ኔትዎርክ) የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የጥናት ሲምፖዚየም በአርጀንቲና የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ሲምፖዚየም ደግሞ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የጥናቱ ሲፖዚየም ዋና ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጀ የእናቶችን እና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ እየተሰጠ ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በማስፋት ብቻ የታለመለትን ያሕል ውጤት ማስገኘት እንዳልተቻለ በጥናት የተረጋገጠ በመሆኑ በቀጣይ የሚሰጡ የእናቶችን እና የሕጻናት ጤና አገልግሎቶች ምን መምሰል እንደሚገባቸው የሚሳዩ ጥናቶች የሚቀርቡበትና አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው፡፡
አቶ እስራኤል አታሮ በጤና ሚኒስቴር የሕብረተሰብ ተሳትፎና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ መሪ ስራ አስፈጻሚ ኃላፊ በሲምፖዚየሙ የመክፈቻ ስነ-ስረዓት ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ከማስተላለፈቸውም በላይ የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ምን እንደሚመስል ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኬኒያ፣ናይጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የማላዊ እና ሶማሌ ላንድ ሀገር የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች በሀገራቸው ያለውን የጤና አገልግሎት አሰጣት አስመልክቶ ገለጻ አድርገው ውይይት የተካሄደ ሲሆን ሌሎችም የኔቶርኩ አባል ሀገራት በሲፖዚየሙ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ጌታቸው የኢንስቲትዩቱ የስርዓተ ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የእናቶችን እና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችል በአዲስ አበባ፣ በሲዳማ እና በሱማሌ ክልሎች የተሰራ የአዋጭነት ጥናት፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡ በስርዓተ ጤናው ላይ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል የሚለውን የሚያሳይ ሀገር አቀፍ ጥናት፣ እንዲሁም ነፍሰጡር እናቶች ከእርግዝና ጀምሮ እስከ ድህረ ወሊድ ድረስ የሚሰጣቸው የጤና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ መሆን አለመሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች በሲፖዚየሙ ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡