ጫት በሃገር አቀፍ ድረጃ እያስከተለ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ አውደጥናት እየተካሄደ ነው
የኢንስቲትዩቱ የስርዓተ ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሮክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከያ ዳይሬክቶሬት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጫትን አስመልክቶ ከየካቲት 16 እስከ 17/ 2012 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በአዱላላ ሪዞርት ሀገራዊ የምክክር ዓውደ-ጥናት እያካሄደ ነው፡፡
የምክክር ዓውደጥናቱ ዋና አላማ ጫት በኢኮኖሚ፣በጤና እና በማህበራዊ ሁኔታዎች ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት የሚያሳዩ የምርምር ስራዎችና ውጤቶች ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለመንግስት እንደግብዓት የሚያገለግል መረጃ ለማጠናቀር የተዘጋጀ የምክክር አውደጥናት ነው፡፡
ዶ/ር ኤባ አባታ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ጫትን አስመልክቶ የተለያዩ ተመራማሪዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የምርምር ስራዎችን መስራታቸውንና በዚህ ዙሪያ በጤና ሚኒስቴር እና በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራር አካላት በርካታ ውይይቶች መደረጋቸውን ከመግለጻቸውም በላይ በጤና ፣በኢካኖሚ እና በማህበራዊ ዙሪያ ጫት እያስከተለ ያለውን ጉዳት በተናጠል ሳይሆን በሁሉም አቅጣጫ እያደረሰ ያለውን ችግር በዚህ አውደ ጥናት ላይ ሞያዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተሰርቶ የሚጠናቀቀው ውጤት ለመንግስት ጥሩ ግብዓት ሊሆን እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን በዝርዝር ተናግረዋል፡፡
ወ/ሪት ሕይወት ሰለሞን የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስለ አውደጥናቱ ዋና አላማና አጠቃላይ የውያይቱን ሂደት ምን እንደሚመስል የግንዛቤ የማስጨበጫ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
በአውደጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን ጫት በሳይንሳዊ ስሙ ካታ ኢዱሊስ አነስተኛ መጠን ያለው እና ባለ አበባ ተክል መሆኑን በምስራቅ አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ በሰፊው የተስፋፋ ስለመሆኑ ጫት በኢትዮጵያ ፤ኬንያ ፣ ሶማሊያ ፣ ጅቡቲ ፣ ኡጋንዳ ፣ ታንዛኒያ ፣ ዚምባብዌ ፣ ዛምቢያ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና በየመን በስፋት እንደሚገኝ ተገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባካሄደው ስር የሰደዱ የማይተላለፉ በሽታዎች ስርጭትና መጠን የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው ዕድሜያቸው ከ15-69 ዓመት ከሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 16 በመቶ ጫት በመቃም ላይ ያሉ መሆናቸውን ከነዚህም መካከል 58 በመቶው ጫትን በየቀኑ ሲቅሙ እንደነበር ጥናቱ ከማሳየቱም በላይ ጫት እየቃሙ የሚያጨሱ 16 በመቶ፣ጫት ከቃሙ በኋላ አልኮል የሚጠጡ 32 በመቶ መሆናቸውንና ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ጫት በሚቃምበት ወቅት ማሕበራዊ ግንኙነቶችን ያሻሽላል ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ተመራማሪዎች እንዳሳዩት ጫት ከፍተኛ የሆነ ስንፍና እና ከስራ ገበታ ላይ መቅረትን በማስከተሉ ሀገራዊ ምርት እንዲያሽቆለቁል በማድረግ የሃገራትን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን እና በዓመት ውስጥ ከ 4 ቢሊዮን ሰዓታት በላይ በጫት ምክንያት እየባከነ መሆኑን በጥናታቸው ያመለከቱ ሲሆን ከ 20 በላይ የሆኑ ሀገራት በጫት ላይ ቁጥጥር እና እገዳ የሚደረግበት ተክል አድርገው መፈረጃቸውን እንዲሁም አብዛኛቹ የአውሮፓ፣ የእስያ፣ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ውስጥ ህገ ወጥ ሆኖ እንደሚታይ ተገልጻል፡፡
በምክክር አውደጥናቱ ላይ ጫት በጤና ፤ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ላይ ያለውን ፋይዳ ፣ የተጠኑ ጥናቶችና ምርምሮችን የመፈተሸ ስራ ፣ የጫት አምራችነት፣ ዝዉዉር እና ሻጭነት እንዲሁም ተጠቃሚነት በሕግ ዕይታ ምን እንደሚመስልና የተለያዩ ሀገራትን የልምድ ተሞክሮዎች የሚታዩበትና ሰፊ ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን በቀጣይ ጫትን አስመልክቶ በሃገር አቀፍ ደረጃ መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎች የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ለመንግስት የሚያገለግል መረጃ በማጠናቀር እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ባስቀመጥ አውደጥናቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከ50 የሚበልጡ የጤናው ዘርፉ ተመራማሪዎች፣መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የስራ ኃላፊዎች የፖሊሲ አውጭ አካላት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የጤና ምርምር ተቋማት፤ የጤና ሙያ ማህበራትና አጋር ድርጅቶች እና በጫት ላይ ለበርካታ ዓመታት ጥናትና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች በምክክር ዓውደ-ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡