ኢንስቲትዩቱ ክልሎች የሕብረተሰብ ጤና ምርምርን እንዲያጠናክሩ የዲጂታል መሠረተ ልማት መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ

September 2, 2026
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ የተገዙ ሰርቨሮችን ለአራት ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች የመረጃ ቋትን፣ ዲጂታላይዜሽን እና የምርምር አቅምን እንዲያጠናክሩ የዲጂታል መሠረተ ልማት መገልገያዎች ድጋፍ አድርጓል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ የ2019 ዓ.ም ዓመታዊው የግምገማ ጉባኤ ጎን ለጎን ክልሎች እራሳቸውን እንዲያጠናክሩና የቴክኖሎጅ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ይህ ድጋፍ እንደተደረገላቸው በመግለፅ፣ ክልሎች መረጃዎቻቸውን በአግባቡ እንዲያከማቹ፣ እንዲተነትኑ እና ለምርምርና ውሳኔ ሰጪ ሥራዎች እንዲያውሉ እንዲሁም በአገር ደረጃ የመረጃ ልውውጥን እንዲያሳልጡ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው ድጋፉ አፋር፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ምርምር እንዲያካሂዱና የጤና ሥርዓቱን እንዲያጠናክሩ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀመዶ አህመድ የተደረገው ድጋፍ የተቋማቸውን የመረጃ ማከማቻ ቋት እና የሕብረተሰብ ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ማዕከልን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።