የኮሌራን በሽታ በማጥፋት የሕብረተሰቡን ጤና፣ የኢኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ አቅም ማበልፀግ

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራን በሽታ በማጥፋት የሕብረተሰቡን ጤና፣ የኢኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ አቅም ማበልፀግ እንደሚቻል ተገለፀ።
————————————
የኮሌራ በሽታን ከመላው ኢትዮጵያ ለማስወገድ ይቻል ዘንድ እየተሠራ እንደሆነ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው ሀገራዊ ዕቅድን በማጠናከር በ2030 ኮሌራን በዘላቂነት ለማስወገድ ባለመው የተቀናጀ የሀገር አቀፍ ጥረትን ለማፋጠን እንዲረዳ በዘርፉ የሚገኙ የሀገር አቀፍ እና የዓለም አቀፍ አጋር አካላት ከፍተኛ አመራሮችን ባሳተፈው የምክክር መድረክ ላይ ነው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኮሌራን በሽታ እና በበሽታው የተነሳ በማህበረሰቡ ላይ የሚከሰቱ በርካታ የጤና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ሌሎችም ተፅዕኖዎችን በዘላቂነት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ የመንግሥት፣ የአጋር አካላት እና የማህበረሰቡ የተቀናጀ ትብብር እና ቁርጠኝነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል ።
አቶ መደሀንዬ ሀብተየስ በኢትዮጵያ የሕበረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽና መልሶ ማገገም ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመንግስት እና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለው ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የሕበረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት የተላላፊ በሽታዎች ወረሽኝ ምላሽና መልሶ ማገገም ዲቪዢን ኃላፊ አቶ በላይነህ ኮኮቤ በበኩላቸው ኮሌራን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት በዓለም አቀፍ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ ይገኛል። የዚህ ዉይይት ዋና አላማም ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመለየት እና ክፍተቶችን ለይቶ በቅንጅት በመስራት ኮሌራን ማጥፋት እንደሆነ ተናግረዋል ።
በመድረኩ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የአለም አቀፍ የኮሌራ ቁጥጥር ግብረ ኃይል እና የአለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ኮሌራን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የሚያደርጉትን ቀጣይ ድጋፍና ቁርጠኝነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በምክክር ስብሰባው የብሔራዊ ኮሌራን ማስወገድ ዕቅድ፣ የአፈጻጸም ሁኔታዎቹና እና የቀጣይ ተግባራት ዕቅዶችን የሚመለከቱ ገለጻዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይቶች የተካሄደባቸው ሲሆን በ2030 ኮሌራን ለማስወገድ የሚያስችል የዘርፈ ብዙ ትብብርን፣ የሀብት አሰባሰብን እና የአፈጻጸም ቅንጅትን የበለጠ ለማጠናከር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ የጋራ መግባባቶች ላይ ተደርሷል።