የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት
የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የህክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል፡፡ሚያዝያ 26 ፣ 2012 ዓ.ም
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ከ220 በላይ የህክምናና የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል ፡፡
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ 19 የተቋማት ዝግጁነት ክፍል አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ መሠለ እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ በቻይና ሁዋን ከተማ ከተከሰተ ጀምሮ በሀገራችንም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች የህክምና መስጫ ማዕከል (Treatment centers) ፣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው እስኪታወቅ ተለይተው የሚቆዩበት (Isolation centers) እንዲሁም ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ግለሰብ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለበት በተላለፈው ውሳኔ መሰረት የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን (Quarantine centers) መለየትና ዝግጁ ማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባና በክልሎች ሙሉ በሙሉ ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ጨምሮ ከ10,000 በላይ ሰዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ40 በላይ ማዕከሎች (Treatment centers) ዝግጁ የሆኑ ሲሆን ከ15,000 በላይ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ100 የሚበልጡ የለይቶ ማቆያዎች (Isolation centers) እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የለይቶ ማቆያዎች (Qurantine center) ተዘጋጅተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የኮቪድ 19 ብሔራዊ የድንገተኛ ማዕከል የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን ክፍል አስተባባሪ ወ/ሮ ኢክረም ሬድዋን እንደተናገሩት ለኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ እና ህክምና ማዕከላት ያሉ የውሀ ሳኒቴሽንና ሀይጅን እንዲሁም ኢንፌክሽንን ከመከላከልንና መቆጣጠር አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ለመሙላት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሀ ልማት ኮሚሽን እና ከአጋር ድርጅቶች በተደረጉ ድጋፎች ሲሆን የውሀ መቆራረጥና እጥረት ያለባቸውን ተቋማት ክፍተት መሙላት፤ የውሀ አቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ የውሀ ታንከሮችና ፓምፖችን መግጠም፣ ውሀን በትራክ ማቅረብ እንዲሁም የእጅ መታጠቢያ እጥረት ባለባቸው የለይቶ ማቆያ እና ህክምና ማዕከላት ከእጅ ንክኪ የጸዱ በእግር መከፈት የሚችሉ ተንቀሳቃሽ የእጅ መታጠቢያዎች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም ለሁሉም ለይቶ ማቆያ እና ህክምና ማዕከላት የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ለሚገኙ የለይቶ ማቆያ እና ህክምና ማዕከላት የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ባለሙያዎች ተመድበዋል፡፡ ለነዚህ ባለሙያዎችም የኮቪድ-19 የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ባለሙያዎቹም በአጠቃላይ የሚከናወኑ ተግባራት ኢንፌክሽንን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በአግባቡ እየተካሄዱ መሆናቸውን በየዕለቱ ይከታላሉ ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚሰሩ ስራዎች ባሻገር ህብረተሰቡ የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለበሽታው ያለመስፋፋት ወሳኝ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት