24 ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ በሃዋሳ ከተማ ተጀምሮአል

“ፍትሃዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል 24ኛው ዓመታዊ የጤና ጉባኤ በሃዋሳ ተጀምሮአል፡፡ የትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኤድስና ቲቢ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርም በጉባዔዬው በጤና ሙያ መስክ ልዩ ስራና የላቀ አገልግሎት መስክ ወ/ሮ ሳሮ አብደላ የዘንድሮው ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በዚህ አመታዊ ጉባዔ ላይ ክብርት የጤና ሚኒስትሯን ጨምሮ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ፣ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ከፊዴራልና የክልል ተቋማት ቢሮ ሃላፊዎች፣የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት፣የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በጉባዔው መክፈቻ ላይ የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ ልዳሞ እንዳሉት የጤና ስራዎች በጣም ወሳኝ እንደመሆናቸው በመንግስትን ጥረት ብቻ ሳይሆን የለጋሽና አጋር አካላትን እገዛ ይፈልጋሉ፣በመሆኑም በዚህ ረገድ እስካሁንም ሲያደርጉ የቆዩትን እገዛ አጠናክረው በመቀጠል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የግሉ የጤና ሴክተር የጤና ተደራሽነትን ለማሳለጥ አመርቂ ስራ ሰርተዋል ያሉት አቶ ደስታ፣ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ በጨቅላ ህጻናት ህክምና፣በኤች አይቪ መከላከል፣በቲቪ፣በወባ፣በአይን ቀዶ ህክምና ፣ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መከላከል ዙሪያ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ አገልግሎት ማሻሻልን ትኩረት ያደረጉ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡በተለያዩ ወቅቶች የተከሰቱ የወረርሽኝ ስጋቶችንም ለመከላከል ውጤታማ ስራ ተሰርቶአል ብለዋል፡፡
የምርምር ስራን በተመለከተ የኢትዮጰያ ሕብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የአርማወ ሃንስን የምርምር ኢንስቲትዩት 185 የምርምር ስራዎች በተለያዩ ጆርናሎች ማሳተማቸውን ጠቅሰው ስድስት የፖሊሲ ብሪፍ ስራዎችም ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ማሻሻያ፣ ጥራትና ፍትሃዊነት ዋና ትኩረት በማድረግ የጤና ስርዓቱን ጠንካራና የማይበገር ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡ለዚህም የሁሉም አካላት ትብብር ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡
በመክፈቻው እለትም በተመረጡ የጤና ተቋማት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና ም/ ዳይሬክተሮችን ጨምሮ የመስክ ጉብኝት ተደርጓል፡፡
በጤና ዘርፍ በልዩ ልዩ አገልግሎቶች የተመረጡ ባለሙያዎች የእውቅና ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ የኤድስና ቲቢ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በጤና ሙያ መስክ ልዩ ስራና የላቀ አገልግሎት መስክ ወ/ሮ ሳሮ አብደላ የዘንድሮው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ 450 ተሳታፊዎች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡