24ኛው የጊኒ ዎርም የማጥፋት ፕሮግራም የግምገማ ስብሰባ ተካሄደ
የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉትን ስራዎች የሚገመግም 24ኛው ሀገር አቀፍ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ትናንት በጋምቤላ ከተማ ከታህሳስ 7-8/2012 ተካሄደ፡፡ የአፍሪካ የጊኒ ወርም በሽታ ማጥፊያ ፕሮግራም የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በእቅድ አፈጻጸም ግምገማው ላይ እንዳሉት፤ የጊኒዎርም በሽታን ከአገሪቱ ለማጥፋት ከአመራሩ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ይጠበቃል፡፡
በተለይም በሽታው በማህብረሰቡ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በአገሪቱ መልካም ገጽታ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የክልሉ መንግስት ለህብረተሰቡ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽ በማድረግና በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሰራተኞች የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲያቀርቡ በማድረግ ረገድ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በሽታውን ከክልሉ ብሎም ከአገሪቱ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለህብረተሰቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ በተለይም ከዚህ በፊት በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የውሃ ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ ለህብረተሰቡ ስለበሽታው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሰራተኞቻቸው ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያቀርቡ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የጊኒ ወርም በሽታን ከአገሪቱ ለማጥፋት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ያስፈልጋል፡፡
በሽታው ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰዎች ላይ ያልተከሰተ ቢሆንም በውሾችና ድመቶች ላይ መታየቱን ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡም በእነዚህ እንስሳት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በሽታውን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ ብሎም ከአገሪቱ የጊኒ ዎርም በሽታ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ በማስቀጠል አገሪቱ ከበሽታ ነጻ መሆኗን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ለማግኘት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
በ24ኛው አገር አቀፍ ዓመታዊ ግምገማ የክልልና የፈዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ደርጅት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በግምገማው ላይ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የፈረንጆች አመት በሽታውን ለመከላከል የተደረጉ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ተቀምጠዋል፡፡