27ኛው ሀገራዊ የጊኒ ዎርም ማጥፋት ፕሮግራም ዓመታዊ ግምገማ ተጀመረ
January 24, 2023
የኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም ማጥፋት ፕሮግራም ዓመታዊ ግምገማ በጋምቤላ ከተማ ጥር 16/2015 የተጀመረ ሲሆን ስብሰባውም ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።
የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮት ጋትዊች በእንኳን ደህና መጣቹህ መልዕክታቸው በቅንጅታዊ አሰራር ላይ የተመሰረተ የጊኒ ዎርም ማጥፋት ላይ የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም ጠንካራዎችን ለማስቀጠልና ደካማ ጎኖችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የስብሰባው ዋና ዓላማ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ታንክዌይ ጆክ የጋምቤላ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር በክልሉ በቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ አለመኖር፣ በክልሉ በዛ ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች በመኖራቸው ከፍተኛ የሰዎች ዝውውር መኖሩ፣ የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶችን በአግባቡ አለመጠቀም የጊኒ ዎርም በሽታ በክልሉ ለበሽታው እንደገና መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በንግግራቸዉ እንደተናገሩት የጊኒ ዎርም በሽታ ትኩረት ከሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች መካከል አንዱ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታውን ለማጥፋት በተደረገው እንቅስቃሴ በብዙ ሀገራት ማጥፋት የተቻለ ቢሆንም አሁንም ግን ሀገራችንን ጨምሮ በ5 ሀገራት እንደሚገኝና በሀገራችን በሽታውን ለማጥፋት ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው አሁንም በቀጣይ አጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ በመስራት በሽታውን ከሀገራችን ማጥፋት እንደሚጠበቅብን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በመልዕክታቸው እስካሁን ከተመዘገበዉ 4,697 በበሽታዉ ከተያዙ ሰዎች በመጀመሪያ አስርተ ዓመታት (እ.ኤ.አ ከ1993-2002) በሰዎች ላይ የበሽታዉ የስርጭት መጠን በ95%፤ በሁለተኛዉ አስርተ ዓመታት ላይ (ከ2003-2013) በ4%፤ በሦስተኛዉ አስርተ አመታት (ከ2014-2022) ከነበረዉ የበሽታዉ ተጠቂ መጠን ከ1% በታች የበሽታዉን ሥርጭት ዝቅ መደረግ ሲቻል በእንስሳት ረገድም ሲታይ እ.ኤ.አ ከ2020 ከተመዘገበዉ በ27 % ያህል መቀነስ መቻሉ ጤና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት፣ ባለድርሻ አካላት እና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት መደረጉን እንደሚያመለክት ገልፀዋል፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ሁሉንም በሽታውን ለማጥፋት በመስራት ላይ ያሉትን አመስግነው በሽታው በኢንስቲትዩቱ ከተለዩ 36 ሪፖርት የሚደረጉ በሽታዎች አንዱ ሲሆን የሚያስከትለው ሞት አነስተኛ ቢሆንም በሕብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው የስነ ልቦና ተፅዕኖ ቀላል አለመሆኑን ከገለጹ በኋላ አያይዘውም የጊኒ ዎርም በሽታ ከሀገራችን ለማጥፋት እንደ በሽታዉ ክስተት አይነትና መጠን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በደረጃ የተለዩ ሲሆን በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠዉ በጋምቤላ የሚገኙ የበሽታዉ ክስተት የተመዘገበባቸዉ አሁንም አዲስ ክስተት ያለባቸዉ ሁለት ወረዳዎች (ጎግ እና አቦቦ)፤ ደረጃ ሁለት የቅርብ ተጋላጭ የሆኑ 14 ወረዳዎች ማለትም ከጋምቤላ(11)፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ(1)፤ ከደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልላዊ መንግስት(1) እና ከኦሮሚያ(1) ሲሆኑ ቀሪዎቹ ወረዳዎች ምንም በሽታዉ ካለባቸዉ አከባቢዎች ጋር ቅርበት የሌላቸዉ መሆኑን አስረድተው በሽታውን ለማጥፋት ሁሉም አካል በባለቤትነት መንፈስ መስራት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።