5ኛው አገር አቀፍ የላቡራቶሪ አገልግሎት የምክክር መድረክ እተካሄደ ነው
የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ እና ከክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ምርመራና ምርምር ላቦራቶሪ ማዕከል ጋር በመተባባር ከየካቲት 13 እስከ 14/2012 ዓ.ም 5ኛውን አገር አቀፍ የላቦራቶሪ አገልግሎት የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ በሴንተራል ሆቴል እያካሄደ ነው፡፡
የምክክር መድረኩ ዋና አላማ በሃገር አቀፍ ደረጃ በላቦራቶሪው ዘርፍ በእቅድ ተይዘው የተሰሩ ስራዎች፣ያጋጠሙ ችግሮች የሚገመገሙበት ሲሆን በቀጣይ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች እና መሰራት ያለባቸው ስራዎች የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ነው፡፡
አቶ አዲሱ ከበደ የኢንስቲተዩቱ የላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት የምክክር መድረኩ በአዲስ አበባ፣በባሕርዳር ፣በአዳማ እና በሰመራ ከተማ በአጠቃላይ ለ4ጊዜ የተካሄደ መሆኑን፣በተካሄዱት መድረኮች በርካታ ትምህርቶች መገኘታቸውን፣በሃገር አቀፍ ደረጃ በጤና ላቦራቶሪዎች የተሻሉ አፈጻጸሞች፣ጥራት ያላቸው የላቦራቶሪ አገልግሎቶች እና ተደራሽነት ማስመዝገብ መቻሉንና እየተካሄደ ያለው የምክክር መድረክ ለ5ኛ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አብደላ ሐሰን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊ በበኩላቸው የላቡራቶሪ አገልግሎት ከህብረተሰብ ጤና አንጻር በተለይም የላቦራቶሪ ጥራትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ የላቦራቶሪ ጥራትን ለማሳካት እና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በትክክል መመራት እንደለበት ለዚህም የምክክር መድረኩ ትልቁን ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአለፈው አመት በጋራ የታቀዱ እቅዶች አፈጻጸም በአቶ አዲሱ ከበደ የቀረቡ ሲሆን ፣ የተመዘገቡ ውጤቶች፣ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ መፍትሄዎች በምክክር መድረኩ ላይ የሚቀርቡ ከመሆናቸውም በላይ ሰፊ ግምገማና ውይይት ተካሂዶባቸው መስተካከል የሚገባቸውን አቅጣጫዎች በማስቀመጥ እንዲሁም ለቀጣይ በላቦራቶሪው ዘርፍ መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮ ላይ የጋራ እቅድ በማውጣት የምክክር መድረኩ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
በብሔራዊ አክሬዲቴሸን ጽ/ቤት በISO 15189 የእውቅና ሰርተፍኬት እና ዋንጫ ያገኙ 23 ላቦራቶሪዎች በምክክር መድረኩ ማጠቃላያ ወቅትም የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ከመድረኩ አስተባባሪዎች ማወቅ ተችሏል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ዳይሬክተሮች እና የላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ የክልል ላቦራቶሪ ሃላፊዎች እና የላቦራቶሪ ጥራት ቁጥጥር መኮንኖች፣የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ላቡራቶሪ ሃላፊዎች እና ከፍተኛ የላቦራቶሪ ትምህርት ቤት ተወካዩች በአጠቃላይ ከ100 በላይ የሚሆኑ በምክክር መድረኩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡