6ኛው የብሔራዊ ላቦራቶሪ ጉባኤ ተጠናቀቀ
በኢንስቲትዩቱ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትብብር የተዘጋጀው ስድስተኛው የብሔራዊ ላቦራቶሪ ጉባኤ በመልካም ሁኔታ በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ላቦራቶሪ አቅም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ከበደ እንደተናገሩት ይህ ጉባዔ በየአራት ወሩ የሚደረግ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከተያዘለት ቀን ትንሽ የዘገየ ቢሆንም አሁንም ባገኘነው አጋጣሚ መልካም እና ገንቢ ውይይት እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው እንዲሁም ባለፈው ሐዋሳ አምስተኛ ጉባዔ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ምን ሁኔታ ላይ እንደደረሱ እንደሚገመገሙ ለቀጣይ የሚፈለጉ ስራዎች አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ከገለጹ በኋላ የድሬዳዋ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ የሱፍ ሰኢድ የእንኳን ደህና መጣቹህ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡
አቶ የሱፍ በበኩላቸው በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውም በጉባዔው የሚቀርቡ የላብራቶሪዎች የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶች፣ በዘርፉ ያሉ አዳዲስ አሰራሮች፣ መልካም ተሞክሮዎችና ስራውን ለመስራት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች እንዲሁም ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማንሳት የመድረኩ ተሳታፊዎች የተላያዩ ልምዶችን የሚቀስሙበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተለያዩ ያጋጠሙ ችግሮች ለምሳሌ ናሙና በፖስታ የማጓጓዝ አገልግሎት በየቦታው አለመኖር፣ የላቦራቶሪ የምርመራ ሪኤጀንቶች በሚፈለገው መንገድ አለመሰራጨት፣ የላቦራቶሪ እውቅና ላይ በጋራ አለመስራት፣ የላቦራቶሪ መሳሪዎች ጥገናን በተመለከተ፣ የግዢ መጓተት እና በየጊዜው ዋጋ መጨመር፣ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የክልል ላቦራቶሪዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ የተለያዩ የሆስፒታል ተወካዮች፣ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ፣ የማረሚያ ቤት፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአፍሪካ ላቦራቶሪ ማህበር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የሚመለከታቸውን ሪፖርቶች በጽሁፍ አቅርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡