የኢንስቲትዩቱና የዩኤስ ሲዲሲ የጋራ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ተገመገመ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (US-CDC) የጋራ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ዓመታዊ ግምገማ የክልል ጤና ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ጥቅምት 11-14 በድሬዳዋ ከተማ ተካሄደ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት ማዕከሉ በ 2001 እ.ኤ.አ ቢሮውን በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ጊቢ ከከፈተ ጀምሮ አራት ጊዜ የተለያዩ ተከታታይ የአምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅዶችን በጋራ በማቀድ ውጤታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል።
ማዕከሉ፣ ኤች. አይ .ቪ ኤድስ እና ቲቢ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር፣ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት እና ቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር ፣እንዲሁም የላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ስራዎችን ለማጠናከር በርካታ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ዶ /ር ጽጌረዳ ክፍሌ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሂደት እንደየአካባቢው ሁኔታ የራሱ የሆኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች የሚኖራቸው እንደመሆኑ እንደዚህ አይነት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የሚደረጉ መድረኮች ደግሞ በጋራ በመስራት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅርፍ ያስችላሉ ብለዋል።
የዩኤስ ሲዲሲ የጋራ ፕሮጀክቶች ባለሙያ ዶ/ር ዳንኤል ጋርሽያ በበኩላቸው በነዚህ ፕሮጀክቶች መልካም አፈፃፀም የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በፕሮግራሙ ላይ በኢንቲትዩቱ እና በክልል ጤና ቢሮዎች በኩል የተሰሩ ስራዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በተነሱ ሀሳቦች ዙሪያም ዋና ዳይሬክተሩ ተገቢውን ምላሽና አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል።