8ተኛዉ አገር አቀፍ የላቦራቶሪ የምክክር ጉባኤ እየተካሄደ ነዉ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልል ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት 8ተኛዉ አገር አቀፍ የጤና ላቦራቶሪ የምክክር ጉባኤ ከሰኔ 27 እስከ 28/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ ነዉ፡፡
የምክክር ጉባኤዉ ዋና አላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቦራቶሪዎችን አፈፃፀም በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነዉ፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር በጉባኤዉ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ተገኝተዉ እንደገለፁት የጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ ያሉ የጤና ተቋማት የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም ጥራት ያለዉ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዉ፤ የጤና አገልግሎቶችን የተሟላ ከሚያደርጉት በርካታ ስራዎች መካከል አንዱ የላቦራቶሪ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መስጠት ሲቻል መሆኑን ከመግለፃቸዉ በተጨማሪ በወረርሽኝ መልክ ለሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተገቢዉን ምላሽ ለመስጠትና የበሽታ ቅኝቶችን በአግባቡና በአስተማማኝነት ለማከናወን ላቦራቶሪዎች የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ አያይዘዉም በአጠቃላይ ሀገሪቷ ጠንካራና አስተማማኝ የጤና ስርዓት በመገንባት ህዝቦቿ ሁሉን አቀፍ ጥራት ያለዉ አገልግሎት፣ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ባማከለ መልኩ ለመስጠትና ከማናቸዉም የጤና ስጋቶች ለመጠበቅ እንዲቻል በሀገራዊ እስትራቴጂዎች የሚመሩ መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ከሚገኙት መካከል አንዱ የላቦራቶሪዎችን አቅም መገንባት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸዉ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቦራቶሪዎችን አቅም በማሳደግ የጤና ተቋማት ጥራት ያለዉ የተሻለ የላቦራቶሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ አለም አቀፍ እዉቅናና ጥራት ያለዉ የላቦራቶሪ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የጤና ላቦራቶሪዎች አቅም በመገንባት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን የጠበቁ የምርመራ አገልግሎቶች መስጠት እንዲችሉ በመደገፍ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓቱን የጤና እንክብካቤና ሕክምና አገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤናና ጤና-ነክ ምርምሮችን በአግባቡ እንዲደግፍ በማስቻል በኩል በርካታ ስራዎች መከናወናቸዉን ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረዉ አብራርተዋል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአፍሪካ ሶሳይቲ ፎር ላብራቶሪ ሜድስን፣የሲዲሲ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ሲዲሲ ተወካዮች በጉባኤዉ ላይ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን አቶ ዳንኤል መለሰ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልል ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ ላቦራቶሪዎችን አስመልክቶ እያከናወናቸዉ ያሉትን ስራዎች በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
በአለም አቀፍ የላብራቶሪ ጥራት አገልግሎት ዕዉቅና ያገኙ የላብራቶሪ ጤና ተቋማት የዋንጫና የዕዉቅና ሰርተፍኬት የተበረከተላቸዉ ሲሆን በጉባኤዉ ላይ የአምስት ዓመት የላብራቶሪ እስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርቦ ትዉዉቅ ከመደረጉም በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ የክልል ላብራቶሪዎች እየተተገበሩ ያሉ የፕሮግራም አፈፃፀም ላይ ዉይይት ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም በላብራቶሪ እስትራቴጂዉ ላይ የተቀመጡ ተግባራት በቀጣይ በተሻለ ስራ ላይ እንዲዉሉ የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ጉባኤዉ እንደሚጠናቀቅ ከጉባኤዉ አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፣የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ኢንስቲትዩት ማኔጅመንት አባላት ለዕዉቅና የተመረጡ የሆስፒታል ኃላፊዎችና ባለሞያዎች የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተወካዮች በመድረኩ በመሳተፍ ላይ ናቸዉ፡፡