አገር አቀፍ የቀዝቃዛ ሰንሰለት መሳሪያዎች (Cold Chain) የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው
የኢንስቲትዩቱ የስርዓተ-ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የክትባት መድሃኒቶች ቀዝቃዛ ሰንሰለት የእቃዎች ዓይነት፣አያያዝ፣ ክምችት እና ስርጭት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃ እንዲሰበሰቡ ለተመረጡ ከ200 በላይ የጤና ባለሙያዎች ከታህሳስ 15 እስከ 17 በቢሾፍቱ ከተማ በስራ አመራር ስልጠና ማዕከል ለሶስት ተከታታይ ቀናት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ ከፌዴራል እስከ ወረዳ በሚገኙ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ላይ የክትባት ቀዝቃዛ ሰንሰለት የእቃዎች ዓይነት፣አያያዝ፣ ክምችት እና ስርጭት በሃገር አቀፍ ደረጃ ምን እንደሚመስል ጥራት ያላቸውን መረጃዎች እንዲሰበስቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ወጪንና ጊዜን ለመቀነስ የውሃ፣ የመንገድና የመብራት የጤና መሰረተ ልማት ዝርጋታ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ከዋናዉ ጥናት ጋር በማቀናጀት መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ እንዲሰሩ ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና ነው፡፡
አቶ አበበ በቀለ የኢንስቲትዩቱ የስርዓተ-ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሰልጣኞችን እንኳን ደህና መጣችሁ መልክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት የጤና ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋታቸውንና ከግብአት አንጻር ግን በትክክል መሟላታቸውን መረጃን መሰረት በማድረግ መፈተሹ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ነው ስለዚህ ጥራት ያለው መረጃ እንድትሰበስቡ ኢንስቲትዩቱም ሃገሪቱም ትልቅ ሃላፊነት ስለሰጧችሁ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ እሳስባለው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ሃላፊ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ኢንስቲትዩቱ በጤናው ዘርፍ ለሃገር እና ለአለም የሚጠቅም ምርምሮችን፣ የላቦራቶሪ ጥራትን የማስጠበቅ እና ሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከል፣የመቆጣጠርና ምላሽ የመስጠት ስራ እንደሚሰራ አብራርተው ገልጸዋል፡፡
የክትባት የቀዝቃዛ ሰንሰለት መሳሪያዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ መረጃዎች መሰብሰብ ያስፈለገበት ምክንያት በሽታዎችን ለመከላከል መሆኑንና ይህ ስራ እጅግ ጠቃሚ እና ለህብረተሰቡ ወሳኝ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ትውልዱን ከተለያዩ በሽታዎች ለመጠበቅ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አንዱ በመሆኑ ጥራት ያለውን መረጃ በመሰብሰብ የዜግነት ሃላፊነታችሁን መወጣት ይገባችኋል ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
አቶ ሃብታሙ ተክሌ የስልጠናው አስተባባሪ በበኩላቸው የስልጠናውን ዋና አላማ እና መረጃ የሚሰበስቡት ባለሙያዎች መረጃ በሚሰበሰቡበት ወቅት የሚያከናውኗቸውን ተግባራትና ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚሰሩ ስራዎችን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የዳሰሳ ጥናቱን መረጃ ለማሰባሰብ የተመረጡት እና እየሰለጠኑ ያሉት የጤና ባለሙያዎች ከ200 በላይ ሲሆኑ ታህሳስ 18/2012 ዓ.ም ወደ ተመደቡበት ቦታ የሚሸኙ ከመሆኑም በላይ ለ3 ወራት የክትባት የቀዝቃዛ ሰንሰለት የእቃዎች ስሪት፣ ብዛታቸው፣ የሚጠቀሙት የሃይል ምንጭ፣ ያሉበት የአገልግሎት ደረጃ ምን እንደሚመስል መረጃ ይሰበስባሉ፡፡
የዳሰሳ ጥናቱ የክትባት የቀዝቃዛ ሰንሰለት የእቃዎች ክፍተት በታየባቸው ቦታዎች ሁሉ መንግስት የውሳኔ ስራ እንዲሰራ ከማድረጉም በላይ በሃገሪቱ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ሰንሰለቱን ጠብቀው በተስፋፉት የጤና ተቋማት ልክ ማቀዝቀዣ መሳሪያዎቹ መኖራቸውን የማሳወቅ እና በቀጣይ ለሚዘጋጀው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ወይም ስር ነቀል መዋቅራዊ እቅድ እንደ መነሻ የሚጠቅም መረጃ ይመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡