ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና (ORCA project) ተሰጠ
የኢንስቲትዩቱ የስረዓተ-ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከለንደን እስኩል ኦፍ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሲን ጋር በመተባበር ከመስከረም 7 እስከ 9 /2012 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በአዱላላ ሪዞርት ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና አውደ ጥናት አካሄደ ፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የእናቶች የጤና አገልግሎት፣ የጨቅላ ህጻናት ሞትን፣ ክትባት፣ አጠቃላይ የህጻናት የምግብ ፣ የወባ እና ቲቢ በሽታ ሁኔታን በተመለከተ በክልልና በሃገር አቀፍ ደረጃ ከጤና ተቋማት በጤና ባለሙያዎች የተሰበሰቡትን መረጃዎች እና የተሰሩትን የተለያዩ ጥናትና ምርምር መረጃዎች የተሰበሰቡበትን እና የተተነተኑበትን ስነ-ዘዴ በመገምገም ለጤና ባለሙያዎች ተገቢውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት በቀረቡት የትንተና ውጤቶች ላይ ተገቢውን የማሻሻያ አስተያየት በማስቀመጥ ለፖሊሲና ለፕሮግራም አውጪዎች አስፈላጊውን አስተያየት በመስጠት የመረጃ ጥራትን ለማሻሻል ታስቦ የተዘጋጀ አውደጥናት ነው፡፡
የጤና ባለሙያዎችን ስለመረጃ አሰባሰብና አተናተን ግንዛቤ ለማስጨበጥና የእውቀትና የክሂሎት ደረጃቸውን ለማጎልበት ከመስራት አንጻር ከዚህ ቀደም ለተከታታይ ስልጠነና የተሰጠ ቢሆንም የአሁኑ ግን የክልሎችንና የሃገር አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ይሰጥ ከነበረው ስልጣና የተለየ እና የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን አቶ ተፈራ ታደለ የኢንስቲትዩቱ የስረዓተ-ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ ገልጸዋል፡፡
አቶ አትኩሬ ደፋር የኢንስቲትዩቱ የስረዓተ-ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ በበኩላቸው ስልጠናውን የተሳተፉ ባለሙያዎች በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የጨቅላ ህጻናትን ሞትና የአመጋገብ ስርዓት፣ የእናቶችን ጤና፣ ክትባት፣ ወባን አስመልክቶ እና ሳንባ ነቀርሳ ላይ ያሉ አጠቃላይ የጤና አገልግሎቶች መረጃ ስርዓት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎችን ሰብስበው ከተለያዩ የጥናት መረጃዎች ጋር በማወዳደር፣ በማነጻጸር ልዩነታቸውንና አንድነታቸውን በመገምገም እና በመተንተን ያዘጋጁትን ጥናትና ምርምር በስልጠናው አውደጥናት ወቅት ያቀረቡ ሲሆን መረጃዎችን የመመዘን እና የመተንተን አቅማቸውን የሚለካ በመሆኑ በአቀረቡት ጥናት ላይ መሰረት በማድረግ አቅም የማጎልበቻ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ አትኩሬ አያይዘውም እንደገለጹት ባለሙያዎቹ ያቀረቧቸው ጥናቶች አስተማሪና ውጤታማ በመሆናቸው በቀጣይ ጤና ሚኒስቴር ባዘጋጀው አመታዊ ጉባኤ ላይ ቀርበው ከታየ በኋላ የክልል ተሳታፊዎች ወደ ክልላቸው ሲመለሱ የመፍትሄ ትግበራው ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት በቀጣይ በጤናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ስልጠናውን የወሰዱት የጤና ባለሙያዎች በክልልና በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጠቀሙባቸውን መረጃዎችን የመሰብሰቢያ ጥያቄዎችንና ጠቋሚዎችን በመጠቀም በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ከጤና ባለሙያዎች እና ከተለያዩ የጤና መዝገቦች የመጀመሪያ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማቀናጀትና በመተንተን በቀጣይ በሚዘጋጀው አውደጥናት ላይ አቅርበው አስፈላጊውን መሻሻል ተደርጎባቸው በአለም አቀፍ ጆርናል ላይ እንዲታተም ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እንደሚሰራም ከስልጠናው አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
ከኢንስቲትዩቱ፣ ከመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እና ከጤና ሚኒስቴር የተመረጡ ከ34 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በአውደጥናቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡