Rabies is Still a Great Public Health Concern
የእብድ ውሻ በሽታ አሁንም አሳሳቢ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳይ ነው
የእብድ ውሻ በሽታ አሁንም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳይእንደሆነ መቀጠሉ የተገለፀው የኢትዮዽያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባክቴሪያል፣ ፓራሳይቲክ እና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት በአዳማ ከተማ ከጥር 6-8/2016 ዓ.ም ባዘጋጃው ስልጠና ላይ ነው።
ስልጠናውን በዋናነት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር ያዘጋጃው UK Health Security Agency (UKHSA) ሲሆን ስልጠናው የተሰጠው ከአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች ለተውጣጡ የጤና ኤክስቴሽን፣ የእብድ ውሻ በሽታ ክትባት እና የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ነበር።
ዶ/ር ይመር ሙሉጌታ የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ተመራማሪ እና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ቡድን መሪ እንደተናገሩት ስልጠናው የኢንስቲትዩቱ እና የእብድ ውሻ በሽታ መከላከል ቴክኒካል ኮሚቴ እንዲሁም በብሔራዊ አንድ ጤና የ2016 ዓ.ም የተግባር ዕቅድ ውስጥ የተያዘ ነው። ይህም በ 2030 የእብድ ውሻ በሽታን ፈጽሞ ለማጥፋት ወይም ዜሮ የሞት ሪፖርትን ለማሳካት የሚያስችል ሀገራዊ አቅምን ለመገንባት ነው።
የUKHSA ተወካይ ዶ/ር ባየህ አሸናፊ ስለ ስልጠናው አጠቃላይ ዓላማና ከስልጠናውም ምን እንደሚጠበቅ ከገለፁ በኋላ ለሰልጣኞች የቅድመ ስልጠና ፈተና ተሰጥቷል።
የእብድ ውሻ በሽታ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ በዶ/ር ይመር የቀረበ ሲሆን ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጥናቶችም በግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር እና የክትባት ምርት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ሠልጣኞችም በቡድን በቡድን በመሆን ተወያይተው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
የባክቴሪያል፣ ፓራሳይቲክ እና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው ስልጠናው በየደረጃው መቀጠል እንዳለበትና ሠልጣኞች የሰለጠኑትን ወደሚሄዱበት ቦታ በመወስድ ለሌሎች ማካፈልና በታቻላቸው መጠንም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመጨረሻም ለሰልጣኞች የእውቅና ሰርተፍኬት እና የMultisectoral Zoonotic Disease Outbreak Investigation መመሪያ መጽሐፍ ተሰጥቷቸዋል።