“ታላቁ ስኬታችን ያለፈው ታሪካችን ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ የምንገነባው የወደፊት እጣ ፈንታችንም ነው”

“ታላቁ ስኬታችን ያለፈው ታሪካችን ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ የምንገነባው የወደፊት እጣ ፈንታችንም ነው” ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት ክብረ በዓልና 5ኛው የሕብረተሰብ ጤና ሳይንሳዊ ኮንግረስ በሳይንስ፣ በፈጠራ እና የወደፊት ራዕይን በሚያመላክት መርሀግብር ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን እና 5ኛውን የሕብረተሰብ ጤና ሳይንሳዊ ኮንግረስ ከሀምሌ 9 እስከ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በድምቀት አክብሮ አጠናቋል። በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችና የጤና ዘርፍ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱ ያለፉት 100 ዓመታት ስኬቶች ከመዘከራቸው በተጨማሪ የቀጣዩ 100 ዓመት ራዕይ በስፋት ተቀምጧል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በመዝጊያ ንግግራቸው፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሕብረተሰቡ ጤና ፣ በጤና ምርምር፣ በላቦራቶሪ አቅም ግንባታ፣ በወረርሽኝ ቅድመ መከላከልና ቁጥጥር፣ እንዲሁም በሀገራዊ የጤና ደህንነት ሥርዓት ግንባታ ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ተቋሙ በጤናው ዘርፍ የልህቀት ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና የዓለም ኩራት መሆኑንም አስረድተዋል።
ዶ/ር ደረጀ አክለውም፣ የኢንስቲትዩቱ ታላቁና አጓጊው የሥራ ምዕራፍ ገና ወደፊት እንደሚጻፍ በመግለጽ፣ ቀጣዩ 100 ዓመት ጉዞ በአራት ዋና መርሆዎች ላይ መመስረት እንዳለበት አስገንዝበዋል። እነዚህም መቀናጀት ፣ መፍጠን ፣ ፈጠራ እና መዝለል መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እየተባባሱ የሚሄዱ እንደ ፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት መቋቋም (AMR)፣ ድንገተኛ ወረርሽኞች እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም በፈጠራ፣ በምርምር እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን አሰራር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስቴር በኢንስቲትዩቱ የዘመናት ጉዞ ላበረከተው የላቀ አመራር፣ ቁርጠኛ ድጋፍና አጋርነት ከኢንስቲትዩቱ ልዩ እውቅና ተሰጥቶታል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው፣ 100ኛውን ዓመት ማክበር ታሪካዊ እድልና ትልቅ ኩራት መሆኑን ገልጸው፣ ተቋሙ በአንድነት፣ በትጋትና በፍቅር ለ100 ዓመታት የገነባውን ታሪክ በቀጣዮቹ 100 ዓመታት የበለጠ ከፍታ ለማድረስ ከአመራሩ እስከ ሠራተኛው ድረስ ቁርጠኞች መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከመንግስት የተሰጡ ተልእኮዎችን ኢንስቲትዩቱ በብቃት እየፈጸመ እንዳለ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የልህቀት ማእከል ለመሆን የተያዘው ራእይም እየተሳካ መሆኑን አስረድተዋል:: ባለፈት መቶ ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶችምን እንደ ግብዓት በመውሰድ ለተሻለ የሕብረተስብ ጤና እንደሚሰራ ገልጸዋል::
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው፣ የኢንስቲትዩቱ የወደፊት እድገት ከዲጂታል ሽግግርና ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አጠቃቀም ጋር በቅርበት የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ግርማ በበኩላቸው፣ የAI ቴክኖሎጂ አጀማመር፣ እድገትና በጤናው ዘርፍ እየፈጠረ ያለውን ለውጥ በዝርዝር አቅርበዋል። የAI አጠቃቀም በበሽታ ቅድመ ትንበያ፣ በምርምር፣ በመረጃ ትንተና እና በውሳኔ አሰጣጥ ውጤታማነትን በማሳደግ ጠቃሚ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
በሳይንሳዊ ኮንግረሱ ወቅት የተለያዩ የምርምር ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን፣ የጤና ሥርዓቱን ውጤታማነት የሚመለከቱ ጥናቶች በአቶ አሸንፍ ታደለ እና በካናዳ የማክማስተር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ዳዊት ወልዳይ ቀርበው፣ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥና የመረጃ ምንጮችን ማጠናከር ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የኢንስቲትዩቱ አዲስ ብራንድ እና 100 ዓመት ታሪክን የሚያስቃኝ መጽሐፍ ተመርቀው ለእንግዶች የተበረከቱ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱን የ100 ዓመት ጉዞ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልምም ቀርቧል።
በማጠቃለያው የ100ኛ ዓመት በዓልንና 5ኛውን የሳይንሳዊ ኮንግረስ በስኬት ላጠናቀቁ አዘጋጅ ኮሚቴዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችና ለበዓሉ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።
ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ “ታላቁ ስኬታችን ያለፈው ታሪካችን ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ የምንገነባው የወደፊት እጣ ፈንታችን ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቀጣዩ 100 ዓመት ጉዞ ከዛሬ ጀምሮ በሳይንስ፣ በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ እና በጠንካራ ትብብር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።