ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርን ይበልጥ እያዘመነች ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ከፌዴራል እና ከክልል ለተውጣጡ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ነው። ስልጠናው የኢትዮጵያን የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር፣ የበሽታ ክትትልና የወረርሽኝ ምላሽ ሥርዓቶችን ለማዘመን የተነደፈ እና አዲስ የዲጂታል መድረክን በአግባቡ ለመጠቀም ክህሎቶችን ለማዳበር ያለመ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች እና ወረርሽኞች ምላሽ በመስጠትና የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅእኖች በመቀነስ ረገድ እያስመዘገበች ያለውን ስኬት ጠቅሰው ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ሥርዓት ለመገንባት እና ለማዘመን ስልጠናው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው ባደረጉት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ሥርዓትን ማሻሻል ከጠቅላላ የጤና ሥርዓት ማዘመን ጋር የተጣጣመ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይህንን ተነሳሽነት በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ እንደዚህ አይነት የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ዶ/ር ሰናይት በዓለም ጤና ድርጅት የኢንፎርሜሽን እና ስጋት አስተዳደር ቡድን መሪ በበኩላቸው የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ሥርዓትን ማዘመን እና ማዕከሉን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ከታቀደው ዕቅድ ውስጥ አንዱ በመሆኑ ይህ ስልጠናው ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው ዲጂታል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓት የተለያዩ ሀገራት እየተጠቀሙበት ሲሆን ሀገራት ካላቸው የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ስርዓት ጋር የሚስተካከል እና በሀገር ውስጥ የመረጃ ቋት ላይ የሚቀመጥ በመሆኑ ተመራጭ አድርጎታል፡፡
ስልጠናው የሕብረተሰብ ጤና ክስተቶችን በአፋጣኝ ሪፖርት ለማድረግ፣ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ስርዓትን ለማዘመን፣ ወረርሽኞችን፣ የግብአት አቅርቦትንና እየተወሰዱ ያሉ የምላሽ እርምጃዎችን ለመከታተል ያስችላል። ይህ ፈጣን፣ ትክክለኛ እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥን ብሎም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ለመለየት፣ የወረርሽኞችን ትንበያና የእርምጃዎችን ውጤታማነት ለመገምገም ይረዳል።
ይህ ዲጂታል መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖረውን ግንኙነትና ትብብርን ያመቻቻል፣ ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት፣ የተሻሻለ የግብዓት አስተዳደር እንዲኖር ያደርጋል፣ ለተሻለ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነትና ተጠያቂነት እንዲሁም ግልጽነትን ያረጋግጣል ተብሎ ታምኖበታል።