ኢንስቲትዩቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም እያጠናከረ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም እያጠናከረ ነው::
ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (NCDs) ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያላትን አቅም ለማጠናከር የሚያስችላትን ስርአት በመዘርጋት አስፈላጊ የሆነውንና፣ የSPARK–NCD የመጀመሪያ ደረጃ የፊልድ ኤፒዲሚዮሎጂ ስልጠና (Frontline Field Epidemiology Training Programme) ተመራቂዎችን በማሰልጠን አስመርቃለች።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ፣ ከልብ ህመም፣ ከስኳር በሽታ፣ ከካንሰር፣ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እና ከአእምሮ ጤና ህመምና መሰል ዕክሎች ጋር የሚመጣው ጫና እየጨመረ መሆኑን በመግለፅ ይህንን ተግዳሮት ለመቋቋም ብቁ የሆኑ የህዝብ ጤና ባለሙያዎች በማፍራት፣ ጠንካራ የበሽታ ክትትል ሥርዓት መዘርጋት እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ዶ/ር ደረጄ እንደገለጹት፣ ጥራት ያለው መረጃ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎች:- በሽታን ለመከላከል፣ ፖሊሲ ለማዘጋጀት፣ ስልታዊ እቅድ ለማውጣት እና ሀብትን በአግባቡ ለመመደብ ወሳኝ መሆ ናቸውን ጠቅሰው፣ ተመራቂዎቹ በኢትዮጵያ የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምላሽ አሰጣጥ ላይ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን የህዝብ ጤና የሰው ኃይል አቅም ለማሳደግና ለማጎልበት ታሪካዊ እምርታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ የመጀመሪያ ደረጃ የፊልድ ኤፒዲሚዮሎጂ ስልጠና በመስጠት 1,581 ባለሙያዎች መሰልጠናቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ ጋር በመሆን የአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) የSPARK–NCD ፍሮንትላይን ፕሮግራምን ለመተግበር ከተመረጡ አራት አገራት መካከል መሆኗን ገልጸዋል።
ይህ ፕሮግራም የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክትትልን ከፊልድ ኤፒዲሚዮሎጂ ስልጠና ጋር በማቀናጀት በሀገሪቱ ያለውን የበሽታ ቁጥጥርና የምላሽ አቅም የበለጠ እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል።
የኢንስቲቱዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው፣ የፊልድ ኤፒዲሚዮሎጂ ስልጠናን የበለጠ ለማጠናከርና መሰል ፕሮግራሞችን ለማስፋፋት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። ተመራቂዎቹም ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባትና በመላ አገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና 18 አስራ ስምንት ባለሙያዎች በበሽታ ክትትል፣ በኤፒዲሚዮሎጂ ምርመራ፣ በመረጃ ጥራት ግምገማ፣ በሳይንሳዊ ተግባቦት እና በማስረጃ ላይ በተመሰረቱ የህዝብ ጤና እርምጃዎች ዙሪያ የተሰጠውን የሦስት ወራት በተግባር ልምምድ ላይ ያተኮረ ስልጠና በተሳካ ሁኔታ አጠናቀው መመረቃቸውን የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ጃፈር ከዛሊ ገልጸዋል
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የSPARK–NCD ፕሮግራሙን ከአፍሪካ ሲዲሲ ባገኘው ድጋፍ ፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ እና አጋር አካላት ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ ድጋፍ ተተግብሯል።